ቀጥታ፡

በሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ጀልባዎችን ማስገባት ተጀምሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦ በሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ጀልባዎችን ማስገባት መጀመሩን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር)፤ በ2017 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት እንቅስቃሴ ላይ የፈጠሩትን ጫና በመቋቋም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር በ2017 በጀት ዓመት 101 ነጥብ 86 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ108 ነጥብ 78 ቢሊየን ብር ገቢ  መገኘቱን ገልጸዋል። 

ይህም ከእቅዱ አንፃር ሲታይ አፈፃፀሙ 107 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።

የድርጅቱ ገቢ ከፍ እንዲል ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ተቋሙ ወጪ ቆጣቢ አሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩም አክለዋል።

በጭነት አስተላላፊ ዘርፍም ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ዓመት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በመልቲ ሞዳል እና በዩኒ ሞዳል ዘርፍ አመርቂ ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል። 

በዚህም ተቋሙ የኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድ በማሳለጥ በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

በሀገር ወስጥ የውሃ ትራንስፖርትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት ዘመናዊ የውሃ ትራንስፖርት ጀልባዎች ማስገባት መጀመሩን ገልፀዋል።

ጣና ነሽ ሁለት እና አንድ ሌላ ተጨማሪ አነስተኛ ጀልባ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ጣናነሽ ሁለት በአሁኑ ሰአት ወደ መዳረሻዋ እየተጓጓዘች እንደምትገኝ አንስተዋል።

እነዚህ ጀልባዎች ቦታቸው ላይ ሲደርሱ ማህበረሰቡን በዝቅተኛ ዋጋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

እንዲሁም ለውጭ ሃገር ጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም