የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ብቁ እና ተወዳዳሪ ትውልድን ከማፍራት ባለፈ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ብቁ እና ተወዳዳሪ ትውልድን ከማፍራት ባለፈ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው
አምቦ ፤ሐምሌ 21/2017 (ኢዜአ)፦ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማሩ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድን ከማፍራት ባለፈ በማህበረሰብ አገልግሎት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በመምህራንና ሠራተኞች በተቋቋመው "ኡቡንቱ" የተሰኘ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ማህበር በኩል በአካባቢው ለችግር የተጋለጡ ወገኖች የህክምና እና የማእድ ማጋራት ድጋፍ እያደረገ ነው።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የማህረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ሙሉ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ጥራት ትኩረት በመስጠት ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ይደግፋል።
በማህበረሰብ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የህግ ምክር አገልግሎትና ልጆቻቸውን ማስተማር ላልቻሉ ወላጆች የትምህርት ቁሳቁስ ከማቅረብ ባለፈ ማእድ ማጋራቱንም አስታውሰዋል፡፡
ለተግባራዊነቱም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞችን በማስተባበር "ኡቡንቱ" የተሰኘ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ማህበርን በማቋቋም በአካባቢው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የህክምና እና የማእድ ማጋራት እያደረግ መሆኑን አንስተዋል።
የኡቡንቱ ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጊፍቲ ደምሴ በበኩላቸው ማህበሩ በአምቦ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ500 በላይ ዜጎች ሰርተው እንዲለወጡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ማህበሩ በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የገንዘብ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በጎ አድራጎት ማህበሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በአምቦ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ገንዘብ ከመደገፍ በተጨማሪ ዘይትና ዱቄት እንዲሁም የህይወት ክህሎት ስልጠና መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡
ከበጎ አድራጎት ማህበሩ ድጋፍ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ዘክራ ዋዩ በሰጡት አስተያየት ማህበሩ በሰጣቸው 7ሺህ 900 ብር ድጋፍ በአነስተኛ ንግድ ላይ በመሰማራት ሁለት ልጆቻቸውን ከማስተማር ባለፈ ከንግድ ትርፋቸው መቆጠባቸውን አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበሩ ለልጆቻቸው የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁሶች ማቅረቡንም አክለዋል።
ሌላዋ በከተማው የማህበሩ ድጋፍ ተጠቃሚ ወይዘሮ መሰረት ከበደ በበኩላቸው የበጎ አድራጎት ማህበሩ ባደረገላቸው 9ሺህ 500 ብር ድጋፍ አነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው አራት ልጆቻቸውን ማስተማራችውን ገልጸዋል።
ማህበሩ የትምህርት ቁሳቁስ፣ ዱቄትና የምግብ ዘይት በመስጠት እየደገፋቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላዋ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰናይት አቦዬ ማህበሩ ለልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁስ እና የ7ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጎላቸው በእንጀራ ንግድ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።