ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦የአብሮነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
ግድቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክትን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል ልምድ የተቀሰመበትና ለሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት የሚጥል መሆኑንም የምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል በምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው ዋሌሬ የግድቡ ግንባታ ሀገራዊ ልማትን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችን በመቋቋም በቁርጠኝነትና በአይበገሬነት መሰራቱ ለትውልዱም በፈተና ውስጥ ለሀገር እድገት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ጌታሁን ነጋሽ በበኩላቸው፣ የግድቡ ግንባታ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በራሳቸው በማዋጣትና ህብረተሰቡን በማስተባበር የዜግነት ሀላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።
የሕዳሴው ግድብ እናቶች ጭምር ከመቀነታቸው ቀንሰው ያሳኩት የልማት ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አሌይካ ሽኩር ናቸው።
ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።
በቀጣይም ለሀገራዊ እንድነትና ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ላይ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።
ከብታቸውን ሽጠው ቦንድ በመግዛት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግም ሌላው የምክር ቤቱ አባል አርሶ አደር ሃጅ ገራድ ተታ ሙዜ ናቸው።
በቀጣይም የተጀመረው ሀገራዊ እድገት ከዚህም በላይ እንዲፋጠን የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።