የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በ2017 በጀት ዓመት ከ108 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በ2017 በጀት ዓመት ከ108 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በ2017 በጀት ዓመት ከ108 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፤ በ2017 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠት እና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር በ2017 በጀት ዓመት 101 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ108 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። ይህም ከእቅዱ አንፃር አፈፃፀሙ ከመቶ ፐርሰንት በላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት እንቅስቃሴ ላይ የፈጠሩትን ጫና በመቋቋም ውጤታማ ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።