ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ላይ ተሞክሮዋን የምታቀርብበት የጎንዮሽ ሁነት ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ላይ ተሞክሮዋን የምታቀርብበት የጎንዮሽ ሁነት ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2017(ኢዜአ)፦ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
የስርዓተ ምግብ አካታችነት፣ የጋራ ተጠያቂነትና ኢንቨስትመንት የጉባኤው ዋንኛ ትኩረት ማዕከሎች ናቸው።
ከዋናው ጉባኤ በተጓዳኝ 31 የጎንዮሽ ሁነቶች ይካሄዳሉ።
ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከሚከናወኑት 31 የጎንዮሽ መድረኮች መካከል ሁለቱ በኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪነት የሚካሄዱ ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) ጋር በመተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ የምግብ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልግ ኢንቨስትመንትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት አዘጋጅተዋል።
ዛሬ የሚካሄደው ሁነት ኢትዮጵያ የግብርና ምርትን ከኢንዱስትሪ ሂደት ጋር በማስተሳሰር የግብርና ጥሬ ግብዓቶችን ወደ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች በመቀየር የምግብ ስርዓቱን ለመለወጥ የያዘችውን ግብ፣ ለውጥ እና አቅም የሚያሳይ እንደሆነ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።
መንግስት ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች(አግሮ ኢንዱስትሪ) ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች እንደሚቀርቡም ተመድ አስታውቋል።
ዲጂታላይዜሽንና ግብርናው የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የግብርና ምርቶችን እሴት ከማሻሻል፣ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ እና የገበያ ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ያላቸው ሚናም ይዳሰሳል።
በውይይቱ ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት፣ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ይሳተፋሉ።