የጉባኤው ዋና ቀናት - ኢዜአ አማርኛ
የጉባኤው ዋና ቀናት
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የጉባኤው የመጀመሪያ ቀን የተግባር ቀን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ስራዎቿንና ተሞክሮዋን ለተሳታፊዎች ያሳየችባቸው የመስክ ምልከታዎች ተደርገዋል።
መልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል እና ሞጆ የዶሮ እርባታና አቮካዶ ማቀነበሪያ ጉብኝት ከተደረገባቸው መካከል ይገኙበታል።
የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶም የተለያዩ ሁነቶች ተከናውነዋል።
ኢትዮጵያ እና ጣልያን የአፍሪካ የቡና ስርዓትን አስመልክቶ ያዘጋጁት ከፍተኛ የምክክር መድረክ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዶ የኢትዮጵያ ልዩ የቡና አፈላል ስነ ስርዓትም ለታዳሚያን ቀርቧል።
ወጣቶች እና ኪነ-ጥበብ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን እውን ከማድረግ በኩል ያላቸውን ሚና የተመለከተ ውይይትም ተደርጓል።
ዛሬ እና ነገ ዋናው የጉባኤ ቀናት ናቸው።
የምግብ ስርዓት ጉባኤው በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በጣልያን ሮም የተካሄደው የመጀመሪያ የተመድ የምግብ ስርዓት ላይ የተገቡ ቃሎች ትግበራ ሂደትን መነሻ በማድረግ የሚካሄድ ነው።
በጉባኤው ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ ያገኟቸውን ስኬቶችና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ።
በተለይም የምግብ ስርዓት ሽግግሩ ሁለንተናዊነት እና ሁሉን አሳታፊነት ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ሁለተኛው የጉባኤው አጀንዳ በመንግስታት፣ የምግብ አምራቾች፣ የንግድ ማህበረሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር ነው።
የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው ታምኖበታል።
በተጨማሪም ሀገራት እና ተቋማት በሮሙ ጉባኤ የገቧቸው ቃሎች የደረሱበትን ደረጃ የሚገመገም ሲሆን ቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ለምግብ ስርዓት ሽግግር የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋትና የኢንቨስትመንት መጠንን መጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም በጉባኤው ይመከራል።
ለምግብ ስርዓት ሽግግር ስራዎች በአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ፣ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም እና ሀገር በቀል የፋይናንስ መሰብሰብ አቅምን ማጎልበት ላይ ምክክሮች ይደረጋሉ ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በሮም በነበረው ጉባኤ ይፋ ያደረጓቸው ስድስት የትኩረት መስኮች አፈጻጸም ግምገማ ሌላኛው አጀንዳ ነው።
በአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተመድ የምግብ ስርዓት ጉባኤ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አርሶ አደሮች፣ አምራቾችና የምግብ ስርዓት ሽግግር ተዋንያንን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።
በጉባኤው ላይ ከዋናው ሁነት ጎን ለጎን የምግብ ስርዓት ትራስፎርሜሽንና የስርዓተ ምግብ ሽግግርን አስመልክቶ 31 የጎንዮሽ ስብሰባዎች ይደረጋሉ።
ከጎንዮሽ ስብሰባዎቹ ሁለቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና እንስሳት ጤና ጥበቃ ጉዳዮች ያዘጋጀቻቸው ናቸው።
ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ሽግግር ያከናወነቻቸውን ተግባራት አስመልክቶ በጉባኤው ተሳታፊዎች የመስክ ምልከታ ይደረጋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በግብርናው ዘርፍ ባደረገቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ጉባኤውን እንድታስተናግድ የተመረጥችባቸው ምክንያቶች ናቸው።