ቀጥታ፡

እንግሊዝ የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫን ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ አነሳች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2017 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ
ጨዋታ እንግሊዝ ስፔንን በመለያ ምት በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።

ማምሻውን በሴይንት ጃኮብ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ማሪዮና ካሊዴንቴ በ25ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ጎል ስፔንን መሪ ሆናለች።

ከእረፍት መልስ አሌሲያ ሩሶ በ70ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈችው ጎል እንግሊዝን አቻ አድርጓል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሯል።

በጭማሪ ሰዓት ግብ ባለመቆጠሩ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል።

በዚህም እንግሊዝ 3 ለ 1 በማሸነፍ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫን አሸንፋለች።

እንግሊዝ ከሶስት ዓመት በፊት  ያዘጋጀችውን 13ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ማንሳቷ የሚታወስ ነው።

በአውሮፓ ኃያላኑ ፍልሚያ ስፔን በኳስ ቁጥጥር ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደች ሲሆን የግብ እድል በመፍጠር ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ ነበሩ። 

የዓለም ሻምፒዮኗ ስፔን በጭማሪ ሰዓት ያገኘቻቸውን እድሎች አለመጠቀሟ ዋጋ አስከፍሏታል።

የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ እና የአዕምሮ ጥንካሬ እንግሊዝን አሸናፊ አድርጓታል።

እንግሊዝ የአውሮፓ ዋንጫ ክብሯን አስጠብቃለች።

ስፔን የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ የማንሳት ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።

እንግሊዝ ከዋንጫው በተጨማሪ የ1 ነጥብ 75 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ታገኛለች።

ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ስፔን 
የ860 ሺህ ዩሮ ተሸላሚ ሆናለች።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የ41 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት ያከፋፍላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም