ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ የተግባር ቀን በሚል ስያሜ ዛሬ ተጀምሯል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ሽግግር እያከናወነቻቸው የሚገኙ ተግባራትን በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በሳይንስ ሙዚየም የአፍሪካን የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግር ማሳደግ ላይ ያለመ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

ለቡና ምርት፣ ማቀነባበር እና ንግድ ሂደት የሚያስፈልግ ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን መፍጠርና ቴክኖሎጂን ማስፋት በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑ ነው በመድረኩ የተነሳው።

በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ፣  የዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፖ፣ የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የጣሊያን ውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የልማት ትብብር ዳይሬክተር ጄነራል ስቲፋኖ ጋቲ፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለምአቀፍ ተመራማሪዎችና የግል ዘርፉ ተወካዮች ታድመዋል።

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ቡና ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካ የግብርና ምርት ብቻ አይደለም። ከታሪክ፣ ከማንነትና ከኢኮኖሚ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ስትራቴጂክ ምርት ነው።

የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ምርት በማምረት ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በትኩረት መሰራቱንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለው ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑን አብራርተዋል።

የተመድ ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና ጄ. መሃመድ በበኩላቸው፤ ቡና የበርካታ ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ህይወት የተመሰረተው በቡና ምርት ላይ መሆኑን አመልክተው፤ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግና እሴት መጨመር የበርካታ ሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግርን ለማምጣት ፋይናንስና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀምና የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፖ በበኩላቸው፤ ቡና ለዩጋንዳና ለበርካታ አገራት የግብርና ማንነትና የአገር አቀፍ የልማት ግብ አካል ነው።

ዘላቂ፣ አስተማማኝና አካታች የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አገራቸው የተለያዩ እርምጃዎች  እየወሰደች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትም በጥራትም ጨምሯል ነው ያሉት።

የቡና ምርትን በምርምርና ፈጠራ በማገዝ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ አገራቱ በሚያመርቱት ምርት ላይ እሴት ከመጨመር ባሻገር በአስተሻሸግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጣሊያን ውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የልማት ትብብር ዳይሬክተር ጄነራል ስቲፋኖ ጋቲ እንደገለጹት፤ አገራቸው በተለይም ለኢትዮጵያና ለዩጋንዳ የቡና ምርትና ምርታማነት ድጋፍ እያደረገ ነው።

ቡና ለዓለም ኢኮኖሚ ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በትብብር መፍታት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ ፤ ቡና 80 በመቶ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች መተዳደሪያ መሆኑን አንስተዋል።

በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ የአነስተኛ ማሳ አርሶአደሮች በአየር ንብረት ለውጥና ለዓለም የቡና ዋጋ መዋዠቅ፣ ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ ማድረጉንም አመልክተዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግርን ማሳደግ''  በሚል ርዕስ የተካሄደው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያና ጣሊያን መንግስታት፣ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ የዓለምአቀፉና የአፍሪካ የቡና ደርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም