ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ሽግግር እና በሌሎች የልማት መስኮች አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበች ነው-የፋኦ ዋና ዳይሬክተር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ሽግግር እና በሌሎች የልማት መስኮች አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበች ነው-የፋኦ ዋና ዳይሬክተር
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ አካታችና የማይበገር የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ጨምሮ በሌሎችም የልማት መስኮች አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበች እንደምትገኝ የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ ገለጹ።
የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ፣ የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀሲካ አሉፖ እና ሌሎችም የተመድ ሁለተኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊዎች የለሚ ኩራ ግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል፣የደጃዝማች ወንዲራድ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ማዕከል እና የጉለሌ የተቀናጀ የእናቶች እንጀራ መጋገሪያ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፥ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች እንዲሁም ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ፣ አካታችና የማይበገር የምግብ ሥርዓት ሽግግር እየፈጠረች ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አስደማሚ ለውጥ የጠንካራ የመሪነት ብቃት ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከአርሶ አደር ጀምሮ ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ እያደረገ ላለው ስኬት የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የሀገሪቱ ዕድገት ፈጣንና ጥራት ያለው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከተሞች በአጭር ጊዜ አረንጓዴና ፅዱ ሆነው በማየታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ የምታቀርበው ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትምህርት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል አመራር እና የመንግሥት ሁሉን አቀፍ የፖሊሲ ርምጃ ኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትክክለኛው መንገድ ላይ እንድትጓዝ አድርጓታል ነው ያሉት።
የተጀመሩ ሰፊ የስራ እድል ፈጠራ፣የትምህርትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል።