ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፕሮጀክቶች ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት መሰረት የሚጥሉ ናቸው-የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በግብርናው ልማት በምግብ ሥርዓት ሽግግር የጀመረቻቸው ፕሮጀክቶች ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ ገለጹ።

የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ፣ የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀሲካ አሉፖ እና ሌሎችም የተመድ ሁለተኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊዎች የለሚ ኩራ ግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል፣ የደጃዝማች ወንዲራድ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ማዕከል እና የጉለሌ የተቀናጀ የእናቶች እንጀራ መጋገሪያ ማዕከልን ጎብኝተዋል።


 

ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ሁሉን አቀፍ ለውጥ  ለማምጣት  የጀመረቻቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳካት የአምራቾች ሚና ወሳኝ መሆኑን  ጠቅሰው፥ ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበት የገበያ ማዕከል መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተመድ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረት የሚጥሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው ብለዋል።

የተማሪዎች ምገባ የሀገር መሰረት መሆኑን በመግለጽ፣ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከማሳ እስከ ገበታ ድረስ የእሴት ሰንሰለት መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳለጥ የጀመረችው ጉዞ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።

ሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮችን በመቋቋም በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የምታደርው ጥረት ለአፍሪካም አርዓያ የሚሆን አስደናቂ ጥረት ነው ብለዋል።

በስንዴ ምርትና በቡና ያገኘችውን ውጤት በሌሎች ዘርፎች ለመድገም ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ መመልከታቸውን በመጥቀስ፣ የከተሞች ኮሪደር ልማት ስራ ላይ ወጣቶች ሲሳተፉ ማየት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም