ናይጄሪያ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን ለ10ኛ ጊዜ አነሳች - ኢዜአ አማርኛ
ናይጄሪያ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን ለ10ኛ ጊዜ አነሳች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2017 (ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ናይጄሪያ ከመመራት ተነስታ ሞሮኮን 3 ለ 2 በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጊዝላን ቼባክ በ12ኛው እና ሳና ምሱዲ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሞሮኮን 2 ለ 0 መሪ አድርጓል።
ይሁንታ ከእረፍት መልስ ኢስተር ኦኮሮኖኮ በ64ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት እንዲሁም ፎላሼድ ፍሎረንስ ልጃሚሉሲ በ71ኛው እና ጄኔፈር ኢቼጊኒ በ88ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፏቸው ግቦች ናይጄሪያ አሸናፊ ሆናለች።
ጨዋታው የተመጣጣኝ እና ጠንካራ ፋክክር ተደርጎበታል።
ሞሮኮ የ2 ለ 0 መሪነቷን አሳልፋ መስጠቷ ዋጋ አስከፍሏታል።
ውጤቱን ተከትሎ ናይጄሪያ ለ10ኛ ውድድሩን በማሸነፍ የበላይነቷን አጠናክራለች።
ሞሮኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት ህልሟ አልተሳካም።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሽን (ካፍ) ለሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ናይጄሪያ ከዋንጫው በተጨማሪ የአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያበረክታል።
ሁለተኛ የወጣችው ሞሮኮ 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ታገኛለች።
ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ጋና የ350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እና አራተኛ ደረጃን የያዘችው ደቡብ አፍሪካ የ300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።ካፍ በአጠቃላይ ለውድድሩ የ3 ሚሊዮን 475 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
የውድድሩ አጠቃላይ ሽልማት መጠንም በ45 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል።