የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ትሩፋቶች ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ትሩፋቶች ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ
በዓለም አቀፍ ደረጃ 420ሚሊዮን ገደማ ህጻናት በትምህርት ቤት የምግባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፕሮግራሞቹ የምግብ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ በጤና፣ ትምህርት እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ግዙፍ ነው።
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎችን የመማር ምጣኔ በመጨመር በተቃራኒው መጠነ ማቋረጥን በመቀነስ ጉልህ ፋይዳ አለው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋም የሆነው የዓለም የምግብ ፕሮግራም እ.አ.አ በ2030 ሁሉም ህጻናት ጤናማ የምገባ ስርዓት እንዲኖራቸው አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
እ.አ.አ በ2022 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ 82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህጻናት የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንደሆኑ ያመለክታል።
በኢትዮጵያም የትምህርት ቤቶች ምግባ መርሃ ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተተገበረ ያለው መርሃ ግብር የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ፣ የተማሪዎች ቁጥር በየጊዜው እንዲጨምር በማድረግ፣ የትምህርት ውጤትን በማሻሻልና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተለይም በአደጋ ተጋላጭ አካባቢ የሚገኙ ህጻናት የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆናቸው በትምህርት ተደራሽነት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እንዲኖር አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በህዳር ወር 2015 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ገልጸው ነበር።
በአሁን ሰዓት ሀገሪቱ እየመገበች ያለችው የተማሪ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገራት የህዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል እንደሆነም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳጊ ህፃናት ትምህርት ቤት መሄድ ሲገባቸው በዳቦ ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም በወቅቱ አንስተው ነበር።
በአዲስ አበባ ደረጃ የምገባ ኤጀንሲ በማቋቋም ተማሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በ2016 ዓ.ም ባወጣው መረጃ በመዲናዋ ከ800ሺህ በላይ የሚሆኑ የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።
ይህ ስራ በ2016 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ የተከናወነውና በርካታ ሀገራት አባል በሆኑበት የዓለም የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት(School Meal Global Coalition) መድረክ ላይ አዲስ አበባ በሌሎች ሀገራት ልምድ የሚቀሰምባት ሆና እንድትመረጥ አስችሏታል።
እ.አ.አ በ2021 የአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ መርሐ-ግብር በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም ሥነ ምግብ ኮንፍረንስ ላይ በመልካም ተሞክሮነት ቀርቦ እውቅና ማግኘቱ አይዘነጋም።
ከሁለት ዓመት በፊት የሚላን የምገባ ፎረም የመዲናዋ የምገባ ፎረም ምርጥ ተሞክሮ በሚል እውቅና ችሮታል።
የአዲስ አበባ አርአያነት ያለው ተግባር ወደ ሌሎች ክልሎችና ከተሞች እየሰፋ ይገኛል።
የምገባ ፕሮግራሙ ከትምህርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ የትምህርት ግብዓቶችን ተደራሽነት ከማሳደግ እና የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ስራዎች ጋር ተደምሮ የተሻሉ ውጤቶች እየተገኙበት ነው።
የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየፈጠረ ያለውን አወንታዊ ተጽእኖና ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል።
በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም በእንግሊዝ ሀገር የተሰማው መረጃም ይሄንኑ የሚያመላክት ሆኖ ተገኝቷል።
የእንግሊዝ መንግስት የህጻናት ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ሊጀምር መሆኑን መግለጹ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
በቀጣዩ ሳምንት የሚጀመረው መርሃ ግብር በሙከራ ደረጃ በ750 ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዚሃን ዘግበውታል።
በቅርቡ በእንግሊዝ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን የጨበጠው የሌበር ፓርቲ ለመርሃ ግብሩ ማስተግበሪያ 30 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡንም እንዲሁ።
በትምህርት ቤቶቹ የነጻ የምገባ ስፍራዎች ተዘጋጅተው ለተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እንደሚሰጡም ተገልጿል።
የእንግሊዝ የትምህርት ተቋም የምገባ ፕሮግራም መንግስት በህጻናት የእድሜ ክልል ያለውን ድህነት ለማስወገድ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ገልጿል።
የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ብሪጄት ፊልፕሰን ምገባው የመንግስት የለውጥ ትኩረት መሆኑን ገልጸው ለወላጆች ኑሮን ቀላልና ተመጣጣኝ ለማድረግ እንዲሁም እያንዳንዱ ህጻን እድሎችን እንዳያገኝ የሚገድቡ መሰናክሎችን ለማስወገድ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክቷል።
መርሃ ግብሩ ወላጆች ለህጻናት ክብካቤ የሚያወጡትን ወጪ እንዲቀንሱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
የሙከራ መርሃ ግብሩ እስከ እ.አ.አ ጁላይ 2025 እንደሚቆይና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ለመሉ መተግበር እንደሚጀመርም ዘገባዎቹ ይጠቁማሉ።
የትምህርት ማህበራትና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን እርምጃውን በመልካም ሁኔታ የተቀበሉት ሲሆን ለምገባው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ወጪ ማሳደግ እና ዘላቂነቱን የሚያጠናክሩ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል።
በአጠቃላይ የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ላይ እያመጣ ካለው በጎ አሻራ ባለፈ ምርታማ ትውልድ ለመፍጠርና ለአንድ ሀገር እድገትና ልማት ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በስኬት ጎዳናና ለሌሎች አርአያ በሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር በግንባር ቀደምትነት የምትነሳ ሀገር ናት።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር እና የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ያላቸው ትስስር ዘርፈ ብዙ ነው።
የተማሪዎች ምገባ በተለያዩ ቦታዎች አካባቢ በቀል ምግብ የሚቀርብበት መሆኑ ቀጥታ ከምግብ ስርዓት ጋር የተቆራኘ ነው።
ይህም አርሶ አደሮች በተለይም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ለምግብ የሚሆን ሰብል አምርተው ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላል።
ምገባው የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት ምጣኔ የሚጨምር ሲሆን ይህም በህጻናት አካላዊና አዕምሯዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው።
የተማሪዎች ምገባ አደጋዎች ሲደርሱ እና የዋጋ ንረት ሲያገጥም በየአካባቢው ባለው ሀገር በቀል አማራጭ ምግብን በማምረት የማይገበር አቅም ለመገንባት እንደሚያስችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለምገባ የሚውሉ እንደ ማሽላና ዳጉሳ ያሉ በንጥረ ነገር የበለጸጉ እህሎች የአየር ንብረትን ለውጥ የሚቋቋሙ ሰብሎች በመሆናቸው ዘላቂ የግብርና ተግባራትና የአየር ንብረት ለመቋቋም የሚደረጉ ጥረቶችን ይደግፋሉ።
መርሃ ግብሩ የንጥረ ምግቦችን ብዝሃነት በማስፋት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚፈጠሩ የእድገት መባባቶችን በመከላከል የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።
በገጠራማ አካባቢዎች የትምህርት መጠነ ማቋረጥን በመቀነስ ለገጠር ልማትና የማይበገር ስርዓተ ምግብ እንዲገነባ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
በገጠር አካባቢ በቂ መሰረተ መሰረተ ልማት አለመኖር እና የመጋዘን እጥረት ወጥ የሆነ የምግብ አቅርቦት እንዳይኖር በማድረግ በምገባ መርሃ ግብሩ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል።
ዘላቂ ፋይናንስ እና የፖሊሲ ቅንጅት ሌላው በምገባ መርሃ ግብር ላይ የሚታይ ክፍተት ሲሆን በትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው፣ ደህንነቱ የተጠበቀና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
በገጠር መንገድን ጨምሮ የገጠር መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል፣ የምግብ ማከማቻዎችና ማስቀመጫ ስፍራዎችን ጥራት ማረጋገጥ፣ የንጥረ ምግቦች ብዝሃነትን ማስፋት፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ከምገባ መርሃ ግብር ገበያ ጋር ማስተሳሰር፣ የፖሊሲ ቅንጅትን ማጠናከርና ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን መፈለግ ለምገባ ስርዓቱ የበለጠ ውጤታማነት የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
በተማሪዎች ምገባ ስርዓት ውስጥ ያለውን የክትትል፣ ቁጥጥርና አቅም ማሻሻያ አሰራሮችን በየጊዜው ማጠናከር እንደሚገባም እንዲሁ።
በጥቅሉ ሲታይ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ህጻናትን መመገብ ብቻ ግብ ያለው ሳይሆን አጠቃላይ የምግብ ስርዓቱን የማጠናከር ግብ ያለው ተግባርን የሚደግፍ ነው።
በሎጅስቲክስ፣ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና ፖሊሲ ላይ ያሉ ፈተናዎች መፍትሄ ማበጀት ከተቻለ የምገባ መርሃ ግብሩ ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የሚያጠራጥር አይደለም።