ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ የበለጸገውን የጣና እና አካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ታነቃቃለች - ኢዜአ አማርኛ
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ የበለጸገውን የጣና እና አካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ታነቃቃለች
ደብረማርቆስ ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፦ ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ባህር ዳር ከተማ ስትደርስ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ የበለጸገውን የጣና እና አካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደምታነቃቃ ተመላከተ።
ጣናነሽ ቀጥር ፪ ጀልባ የሀገራችን የአንድነትና የጽናት ተምሳሌት ናት ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሽ ተመስገን ገልጸዋል።
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ደብረማርቆስ ከተማ የደረሰች ሲሆን በከተማው ስትደርስ በመላው የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።
ጣናነሽ ቀጥር ፪ ከጅቡቲ ተነስታ ወደ ሀገራችን ከገባች ጀምሮ በየደረሰችበት አካባቢ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደማቅ አቀባበል እየተደረገላት ዛሬ ማምሻውን ደብረ ማርቆስ ከተማ ገብታለች።
የጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ባህርዳር ስትደርስ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ የበለጸገውን የጣና እና አካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴን ማነቃቃት እንደምታስችል ተመልክቷል።
ጀልባዋ ከባህርዳር ጣና ማሪና ወደብ ወደ ጎርጎራ ሪዞርት ጎብኝዎችን በፍጥነት በማጓጓዝ የአካባቢውን ጸጋ መሰረት ያደረገ ሃብት ለማመንጨት የጎላ ድርሻ እንደሚኖራት ተገልጿል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሽ ተመስገን በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ የሀገራችን አንድነትና የጽናት ተምሳሌት ናት ብለዋል።
በአካባቢችን እየተሻሻለ የመጣው ሰላም በፌደራልና በክልል መንግስታት እገዛ ተአምራዊ የሆነ የልማት ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።
ለዚህም በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ማሳያ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ በከተማችን መድረሷ መላው የአካባበቢው ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሰላምን ለማጽናት የሰራው ስራ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የከተማውንና የአካባቢውን ህዝብ በማሳተፍ ሌሎች የልማት ስራዎችን በመስራት ከተማዋን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የጣናነሽ ቁጥር ፪ አስተባባሪ አቶ ሳምሶን ገብረስላሴ በበኩላቸው አስቸጋሪውን ጉዞ በህዝቡ ድጋፍ በማለፍ እዚህ በመድረሳችን ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።
ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲደርሱም የየአካባቢው ማህበረሰብና የመንግስት አካላት ያደርጉላቸው አቀባበልና ያሳዩት ስሜት ድካማችንን እንድንረሳ አድርጎናል ነው ያሉት።
ከከተማ አስተዳደሩ ነዋሪ አቶ አማረ አበበ በሰጡት አስተያየት ጣናነሽ ቁጥር ፪ ወደ ከተማችን መምጣቷ የአካባቢውን የቱሪዝም ዘርፍ ማሳደግ የሚያስችል ነው ሲሉ ገልጸዋል።