የፖሊስ አገልግሎትን በማዘመን ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስ አገልግሎትን በማዘመን ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የፖሊስ አገልግሎትን በማዘመን ተልዕኮን በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽኑ ከተባበሩት ዐረብ ኢሚሬትስ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከዱባይ ፖሊስ ለእጀባ እና ፈጣን መንገድ ትራፊክ ደምብን ለማስከበር የሚያገለግሉ ዘመናዊ የሞተር ሳይክሎችን ተረክቧል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከለውጡ ወዲህ በብዙ መንገድ ራሱን እያዘመነ ነው።
በዛሬው እለትም ይህንን ማገዝ የሚያስችል እና ለእጀባ እና ፈጣን መንገድ ትራፊክ ደምብን ለማስከበር የሚያገለግሉ ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎችን በድጋፍ መልክ መረከቡን ገልፀዋል።
በቅርቡም ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች፣ አካባቢን ለመቃኘት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የፖሊስን አገልግሎትን ለማዘመን የሚያስችሉ አቅሞች እየተፈጠሩ ናቸው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎቹ ነገ በሚጀመረው የሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ለሚመጡ እንግዶች እጀባና የደህንነት ሥራ ለማከናወን የሚውሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።