ቀጥታ፡

በክልሉ የደም ልገሳን ማበረታታት የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ

ሸገር ፤ ሐምሌ 19/2017 (ኢዜአ)፡-  በኦሮሚያ ክልል  በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ  የደም ልገሳን ማበረታታት የሚያስችሉ   ተግባራት  እንደሚከናወኑ  የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሸገር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ዛሬ አካሄዷል።


 

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ደም ለግሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር ቦኮና ጉታ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳው ስራ የሚበረታታ ነው።  

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና የግንዛቤ ትምህርት በማስፋፋት በተከናወነው  ስራ ከ17 የደም ባንኮች ከ106ሺህ  በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።


 

ይህም  የሰው ህይወትን ለመታደግ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በክልሉ የደም ልገሳው በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ፍላጎቱና አቅርቦቱ የማይመጣጠን ስለሆነ ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ  አገልግሎት መረሃ ግብር ላይ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በንቅናቄ የሚሰራ መሆኑን አንስተው፤  በዚህም  31 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የደም ልገሳ ተግባራትን በማስፋፋትና በማጠናከር የደም እጥረት ችግር ለመፍታት በቂ ደም ለመሰብሰብ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ  ርብርብ ይደረጋል  ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ  ደም ለጋሾችን ማበረታታት የሚያስችሉ   ተግባራት   እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ የደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው ፤ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ   የደም እጥረት እንዳይከሰት ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በተለይም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ ከሌሎች ወቅቶች የተሻለ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤  ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን ግንዛቤ በማስፋት በቂ ደም ለመሰብሰብ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሸገር ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ምስጋና ዴሬሳ ፤ በከተማው ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር  የደም ልገሳ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 11ሺህ ዩኒት ደም መሰበሰቡን ጠቅሰው፤ ይህም  ከከተማው ባለፈ ለሌሎች ተደራሽ መሆን መቻሉን አንስተዋል።

ዘንድሮም ተማሪዎችንና ወጣቶችን በማስተባበር ቀጣይነት ያለው የደም ልገሳ እንዲኖር የሚያበረታቱ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በደም እጥረት ችግር በተለይ የወላድ እናቶችና ህጻናትን ህይወት ለመታደግ የበኩላቸውን ለመወጣት ደም መለገሳቸውን የገለጹት ከሸገር ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ወይዘሮ ቀመሪያ የሱፍ ናቸው።


 

በቀጣይነት እንደሚለግሱ ገልጸው፤ ሌላውም ሕብረተሰቡ በተመሳሳይ  እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም