ቀጥታ፡

ለዋናው የስርዓተ ምግብ ጉባኤ መሰረት የጣሉት የቅድመ-ጉባኤ ውይይቶች

አዲስ አበባ ሁለተኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ለመጀመር በዋዜማው ላይ ትገኛለች።

ጉባኤው የዓለም ምግብ ስርዓትን ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር ለውጥ የማምጣት ጥረት አካል ነው።

ከዋናው ጉባኤ ቀደም ብሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት የቅድመ-ጉባኤ ስብስባዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በየአህጉራቱ ቀጣናዊ የዝግጅት ስብስባዎች፣ የወጣቶች እና የሲቪክ ተቋማት ምክክሮች፣ የባለድርሻ አካላት ውይይቶችና ሀገራት ተሞክሮ ያከፈሉባቸው ሁነቶች ተካሂደዋል።

ቅድመ-ጉባኤ ስብስባዎቹ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ።


 

በጣልያን እ.አ.አ 2021 በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የተገቡ ቃል ኪዳኖችን መገምገም የመጀመሪያው አጀንዳ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ጉባኤ የውይይት አጀንዳዎችን መቅረጽ መሆኑን የተመድ መረጃ ያመለክታል።

በእነዚህ የቅድመ ጉባኤ ስብስባዎች ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ስራቸውን አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ያጋጠማቸውን ፈተና እና መልካም ተሞክሮም አጋርተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቀውሶች በምግብ ስርዓት ላይ የደቀኑትን ፈተና እንዴት መሻገር ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።

ለምግብ ትራንስፎርሜሽን የሚያስፈልገውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ ሌላኛው የውይይት አጀንዳ ነበር።


 

ከመንግስት እና የግል ቋት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በተጠናከረ መልኩ ማሰባሰብ እንደሚገባም በጉባኤዎቹ ተነስቷል።

የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ፣ የልማት ፈንዶችና የልማት ባንኮች ድጋፍን ጨምሮ አማራጭ የፋይናንስ ሞዴሎችን መጠቀም እንደሚያስልግም ተገልጿል።

የተመጣጠነ ምግብ እና ጤናን ማዕከል ያደረገ የእርሻ ስራ ማስፋት፣ በምግብ ስርዓት ላይ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ፣ ንግድና የገበያ ተደራሽነት እንዲሁም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አጠቃቀምን ማሳደግ ሌሎች ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች ነበሩ።

በእነዚህ ውይይቶች የምግብ ስርዓት ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም የገለጹባቸው ነበሩ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቅንጅት ማዕከልን ወደ ስራ ያስገባ ሲሆን ማዕከሉ ሀገራት የምግብ ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

ከ100 በላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን አካሄዳቸው ላይ ማሻሻያ አድርገዋል አዲስ የአሰራር ስልትም ቀይሰው አቅርበዋል።

አፈጻጸምን የሚቆጣጠሩ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑንና መረጃን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎች መስጠት የሚያስችሉ መለኪያዎችና አሰራሮች ተግባራዊ መሆን መጀመራቸው የቅድመ-ጉባኤ ስብስባዎቹ ውጤቶች ናቸው።

የፋይናንስ ተቋማትና ለጋሾች ለምግብ ስርዓት ምርምሮች፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶችና ለተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራሞች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

የስርዓተ ምግብ ለውጥ አጀንዳን ከዘላቂ ልማት ግቦች፣ ከብዝሃ ህይወት ጥበቃና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ተወስቷል።


 

ስርዓተ ምግብ ምግብን ከማምረት ባለፈ ሁሉን አቀፍ እይታ እንደሚያስፈልገው የተነሳ ሲሆን የከባቢ አየር ተጽእኖ፣ ማህበራዊ ፍትህና የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያላቸው የቀጥታ ተጽእኖ ሊታይ እንደሚገባውም ተመላክቷል።

የቅድመ- ጉባኤ ሁነቶች ሀገራት፣ ባለድርሻ አካላት፣ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት እንዲሁም የልማት አጋሮች በስርዓተ ምግብ ላይ ያሉ ለውጦችን ለመገምገም፣ ልምዶች ለመለዋወጥና ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደ ማዕቀፍ ሆነው አገልግለዋል።

ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ላይ ያላቸውን ቃል ኪዳን የበለጠ ያጠናከሩበት ሆኖም አልፏል።

በኒውዮርክ፣ በባንኮክ፣ በናይሮቢ እና በሌሎች ከተሞች የተካሄዱ የዝግጅት ስብስባዎች በምግብ ስርዓት ፍትሃዊነትና እኩልነት እንዲሰፍን፣ የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት እንዲጠናከር፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆንና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲጎለብት አስቸኳይ የተግባር እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ቀርቦባቸዋል።

በአጠቃላይ ሁነቶቹ ነገ ለሚጀመረው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ሲሆን ዋና ጉባኤው በአጀንዳዎቹ ላይ በመምከር ለውጥ ፈጣሪ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም