ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተገበረቻቸው መርሃ ግብሮች ውጤታማና ለተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተገበረቻቸው መርሃ ግብሮች ውጤታማና ለተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተገበረቻቸው መርሃ ግብሮች ውጤታማና በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የሮክፊለር ፋውንዴሽን የምግብ መርሃ-ግብር ዳይሬክተር ቤቲ ኪባራ ገለጹ።
የፋውንዴሽኑ የምግብ መርሃ ግብር ዳይሬክተር ቤቲ ኪባራ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፋውንዴሽኑ በሰዎች ደህንነት በተለይ ምግብ፣ ኃይል አቅርቦትና ጤና ዙሪያ እየሰራ ይገኛል።
ፋውንዴሽኑ በአፍሪካም ላለፉት 60 ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ ከአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት(አግራ)ና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የስነ ምግብ ስርዓት ላይ ያተኮሩ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
ከሌሎች አጋሮች ጋር በታዳሽ ኃይልና የሰብል ዝርያዎች ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ማከናወኑንም እንዲሁ።
በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መርሃ ግብሮች እየተተገበሩ መሆናቸው የሚደነቅ ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሻሻል ባለፈ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሚና ያለው በመሆኑ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመደበኛ የእርሻ ወቅት በተጨማሪ በመስኖ ጭምር የስንዴ ልማት እያከናወነች በመሆኑ በአርአያነት እንደሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት እያከናወነችው ያለው ተግባር ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ህብረተሰቡ በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦችን በስፋት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወነቻው ያሉ መርሃ ግብሮች ውጤታማና ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና ጣልያን የጋራ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በስርዓተ ምግብ የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ሀገራት ልምዳቸውን የሚያጋሩበት እንደሆነም ገልጸዋል።