ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልልን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠበቅ ለዘላቂ ልማት ለማዋል ጠንክረን ልንሰራ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠበቅና በመንከባከብ ለዘላቂ ልማት ለማዋል ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

‎"ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ" በሚል መሪ ሃሳብ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት 2ኛው ዙር የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

‎ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በወቅቱ እንዳሉት፤ ክልሉ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት ሊውሉ የሚችሉ ሰፊ የውሃ፣ የመሬት፣ የደንና ሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሉበት አካባቢ ነው።


 

በክልሉ ያሉትን እነዚህን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋዎች ከብክለት በመጠበቅና በመንከባከብ ለዘላቂና ቀጣይነት ላለው ልማት ለማዋል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአካባቢ ብክለትን የሚፈጥሩ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በመሰብሰብና በማስወገድ አካባቢን ጽዱና ለኑሮ ምቹ በማድረግ በኩል የማህበረሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

በተለይም እንደሀገር እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት አካባቢን ጽዱና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለዘርፉ ስኬታማነት ሁሉም ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

በዕለቱ በይፋ ለተጀመረው የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ መርሃ ግብር ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ሕዝቡን አስተባብረው እንዲሰሩም አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህግ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሟላ መልኩ በመተግበር የዜጎችን በንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም በመንግስት እየተተገበሩ የሚገኙት የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የኢኮ ቱሪዝም ልማት ስራዎችን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በዘርፉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

የአካካቢ ብክለት ለብዝሃ ህይወት መመናመንም ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን በመከላከል በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአካባቢ ብክለትን የመከላከሉ ተግባር የሁሉም ዜጋ የእለት ከዕለት እሴት ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብርት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ቻም ኡቦንግ ናቸው።


 

የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ የመድረኩ ተሳታፊዎች የአሌሮ ግድብን ተመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም