ቀጥታ፡

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ19/2017(ኢዜአ)፦ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአዲስ አበባ የሚካሔደውን 2ኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጀተናል!

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጀመረቻቸው ጥረቶች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፤ ለላቀ ስኬትም ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከጣልያን መንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመቀናጀት 2ኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።

ይህም በኹለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሚያጎላ፣ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የጀመረቻቸውን ስኬታማ ተግባራት የሚያበረታታ ነው።

ከዐራት ዓመታት በፊት በመጀመሪያው የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ በምታስተናግደው መድረክ ይገመገማል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ።

ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ጉባኤ ርኃብን ስለማስወገድ እና ምግብ ዋስትና፣ ስለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ምክክር ይደረጋል፤ ቀጣይ መወሰድ የሚገባቸው ርምጃዎችም ይመላከታሉ።

ኢትዮጵያ ጉባኤውን የምታስተናግደው ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብ የማንሰራራት ጉዞን በጀመረችበት ወቅት ነው። ለጉባኤው በተሞክሮነት የምታካፍላቸው በርካታ ስኬቶችም አላት።

በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ ድሎችን አስመዝግባለች።

በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ባለፉት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አብነት ናት። ጉባኤው በሚካሄድበት በዚህ ክረምትም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተጋች ነው።

የሚተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻላቸውም በላይ የምግብ ዋስትናን እና ሥርዐተ ምግብን ለማሻሻል ሚና ያላቸው ናቸው።

የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤን እንድታስተናግድ ለኢትዮጵያ ዕድል መሰጠቱም ይህንን ጅምር ዕውቅና የሚሰጥ ነው።

ኢትዮጵያ ባለብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየገነባች እና ኹለንተናዊ ስኬት እያስመዘገበች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሐምሌ 20-22/2017 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዐት ጉባኤን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች።

በጉባኤው የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ የምግብ አምራቾች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሴቶች ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያም የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ ለውጣ እንግዶችን በላቀ ዝግጅት ለመቀበል ተሰናድታለች። በርካታ ስኬቶቿንም በልምድነት ለማካፈል ተዘጋጅታለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ለዘመናት ያስቀጠሉትን ለኹለትዮሽና ባለብዝኃ ወገን ግንኙነት ትኩረት የመስጠት ልምድ ተጠቅመው ጉባኤውን በላቀ ስኬት ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል።

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም