በክረምቱ ሊከሰት በሚችል ጎርፍ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክረምቱ ሊከሰት በሚችል ጎርፍ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየተደረገ ነው
አዳማ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፡- በክረምቱ ሊከስት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ የጥንቃቄና ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋን ያማከለ የአየር ጠባይ ትንበያ አገልግሎት ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ የአየር ጠባይ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች የሚቲዎሮሎጂ መረጃ በመሰብሰብ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲውል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ ጎርፍና የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የጥንቃቄና ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለውጤታማነቱ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሐምሌ፣ ነሐሴና የመስከረም ወራት የክረምት ዝናብ ወቅት በመሆኑ በከተሞች አካባቢ ሊፈጠር የሚችለው ጎርፍ መከላከል ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።
በአሁኑ የክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
መድረኩም በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የአየር ጠባይ ትንተና እና ትንበያ መረጃን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃን በመድረኩ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ(ዶ/ር)፤ በሐምሌ እና በቀጣዩ ነሐሴ ወራት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የክረምት ዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።
በተለይ አዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በትብብር መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ለ200 ከተሞች የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃ እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።