ከናይጄሪያ እና ሞሮኮ አህጉራዊውን ክብር ማን ይቀዳጃል? 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ እና ሞሮኮ ዋንጫውን ለማንሳት ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት ራባት በሚገኘው ፕሪንስ ሙላይ ስታዲየም ይካሄዳል።

ናይጄሪያ በግማሽ ፍጻሜው የወቅቱን የውድድሩ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 1 በማሸነፍ የፍጻሜውን ትኬት ቆርጣለች።

አዘጋጇ ሞሮኮ በጋና ተፈትና በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ ተጠናቆ ወደ ጭማሪ ሰዓት ቢያመራም ግብ አልተቆጠረበትም።

የዘጠኝ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ባደረገቻቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥታለች። 

በጨዋታዎቹ 11 ግቦችን ስታስቆጥር ያስተናገደችው አንድ ጎል ብቻ ነው። ይህም የናይጄሪያ የማጥቃት እና የመከላከል ጥንካሬ የሚያሳይ ነው።

የ28 ዓመቷ አጥቂ ቺንዌዱ ሌሄዙ በሶስት ግቦች የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ናት።ሞሮኮ  በአፍሪካ ዋንጫው ባደረገቻቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርታለች።

በጨዋታዎቹ ሞሮኮ 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ 6 ግቦችን አስተናግዳለች። የ34 ዓመቷ አንጋፋ አጥቂ ጊዝላኔ ቼባክ አራት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ናት።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም የነበራቸው ብቸኛ ግንኙነት እ.አ.አ ሞሮኮ ባዘጋጀችው 12 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው የተገናኙበት ነው።

በጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች አንድ አቻ ተለያይተው ወደ መለያ ምት ያመራ ሲሆን ሞሮኮ 5 ለ 4 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።

በ61 ዓመቱ ጀስቲን ማዱጉ የሚመራው የናይጄሪያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ልምድ ያላቸው እና ወጣት ተጫዋቾችን አሰባስቦ መያዙ አንዱ የጥንካሬው መገለጫ ነው።ከአንጋፋዎቹ ኢሲሳት ኦሾላ፣ ቺያማካ ናዶዜ እና ኦሲናቺ ኦሃሌ ይጠቀሳሉ።

ሹኩራት ኦላዲፖ፣ ሪንሶላ ባባጂዴ እና ኢስተር ኦኮሮንኮ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ናቸው። የአዕምሮ ጥንካሬ፣ ጨራሽ የአጥቂ ክፍል እና የተከላካይ ክፍል መስመሩ አይበገሬነት የንስሮቹ የጥንካሬ ማሳያዎች ናቸው።

በቁልፍ ተጫዋቾች ላይ ከልክ ያለፈ ጥገኝነት እና  የመሐል ክፍሉ የመፍጠር አቅም ወጥ አለመሆን እንደ ድክመት ይነሳበታል።

በ44 ዓመቱ ስፔናዊ ሆርጌ ቪልዳ የሚመራው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የፍጻሜውን ጨዋታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ማድረጉ ትልቅ የሞራል አቅም ይሆነዋል።

የታክቲክ ስሪቱ ጥብቅ የሆነው ብሄራዊ ቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ የመከላከል ቅርጹን የማይለቅ መሆኑ እንደ ጥንካሬ ይነሳል።

በቴክኒክ ክህሎታቸው የበሰሉ የአማካይ ተጫዋቾች እና የቆሙ ኳሶችን የመጠቀም አቅም ለተጋጣሚ ቡድን የራስ ምታት ናቸው።

ግብ ማስቆጠር ላይ በውስን ተጫዋቾች መንጠልጠሉ እና በራሱ የሜዳ ክልል ተጭኖት ከሚጫወት ቡድን ጋር መቸገር የሞሮኮ ድክመቶች ናቸው።

ናይጄሪያ ጨዋታውን ታሸንፋለች የሚል የቅድሚያ ግምት ቢሰጣትም ጥንካሬዋን በየጊዜው እየጨመረች የመጣችው ሞሮኮ ብርቱ ፍልሚያ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

የ33 ዓመቷ ናምቢያዊት አንትሲኖ ትዋንያንኩያ የፍጻሜውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ትመራለች። 

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሚሰጠውን ሽልማት ወደ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማሳደጉ ይታወቃል። ውድድሩን ለሚያሸንፈው ሀገር የሚሰጠው ሽልማት ከ500 ሺህ ወደ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከፍ ማለቱን ካፍ አስታውቋል። 

በአጠቃላይ ለውድድሩ የ3 ሚሊዮን 475 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታውቋል። የውድድሩ አጠቃላይ ሽልማት መጠንም በ45 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም