ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ የይቻላልና የአይበገሬነት መንፈስን ከፍ ያደረገ ትልቁ ሀብታችን ነው - የክልሉ ምክር ቤት አባላት

ቦንጋ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላልና የአይበገሬነት መንፈስን ከፍ ያደረገ ትልቁ ሀብታችን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

ከግድቡ የተገኘውን ልምድ በሌሎች ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ በመድገም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ መረባረብ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የተገነባው የሕዳሴው ግድብ በመጪው መስከረም ወር እንደሚመረቅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በውጭም በውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን በአይነት፣ በገንዘብና በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ደማቅ አሻራቸውን በማሳረፍ ለዛሬ አድርሰዋል። 

ይህን ሀሳብ የሚጋሩት ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የይቻላልና የአይበገሬነት መንፈስ ከፍ ያደረገ ትልቅ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ነው የገለጹት።

ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ተክሌ ተሰማ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የጋራ ሀብትና የኩራት ምንጭ መሆኑን ይናገራሉ።

የግድቡ መጠናቀቅ ህብረት ካለ የማናሳካው የልማት ፕሮጀክት እንደማይኖር ማሳያ ነው ያሉት አቶ ተክሌ፣ የሕዳሴው ግድብ የሀገርን የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳድግና ኢትዮጵያንም በዓለም መድረክ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ለቀሪ የግድቡ ሥራዎች የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡት አቶ ተክሌ፣ የተጀመረው ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ እንዲፋጠን በግድቡ የታየው ትብብርና አንድነትን በሌሎች ፕሮጀክቶችም ሊደገም ይገባል ብለዋል።

ሌላኛው የክልል ምክር ቤት አባል አቶ ጨነቁ ኮንታር በበኩላቸው የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከዳር በማነቃነቅ ሀገራዊ ስሜትንና አብሮነትን ከፍ ያደረገ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።


 

ግድቡ እንዳይገነባ በርካታ ጫናዎች ሲደረጉ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አንድ ላይ ሆነው አይበገሬነታቸውን በማሳየት ደማቅ ታሪክ የጻፉበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ግድቡ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ መድረሱ የህዝብን የይቻላል መንፈስ ማሳደጉንና በቀጣይም ለጋራ አጀንዳ በአብሮነት መቆም ከተቻለ ጫናዎችን ተቋቁሞ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚቻል ትምህርት ተወስዶበታል ብለዋል።

የሕዳሴው ግድብ ጀምረን መጨረስ እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት ትልቁ የጋራ ሀብታችን ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዳዊት ተሰማ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ናቸው።


 

እሳቸው እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠላቸው የግድቡን ግንባታ ከጫፍ ማድረስ ተችሏል።

የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ የማንደራደርና ጠንካራ አንድነት እንዳለን አንድ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

በቀጣይም ሀገራዊ እንድነትን በማጠናከርና ችግሮችን በራስ አቅም በመፍታት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም