ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምስቱ የስርዓተ ምግብ የድርጊት መከታተያ መስኮች ያላት አፈጻጸም ምን ይመስላል? - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምስቱ የስርዓተ ምግብ የድርጊት መከታተያ መስኮች ያላት አፈጻጸም ምን ይመስላል?
እ.አ.አ በ2021 በጣልያን ሮም የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎች የተላለፉበት እና ቃል ኪዳኖች የተገቡበት ነበር።
ተመድ በወቅቱ ሀገራት የምግብ ስርዓታቸውን በማጠናከር የዘላቂ ልማት ግቦችን የማሳካት አቅማቸውን ያሳድጋል ያለውን አምስት የድርጊት መከታተያ መስኮች ይፋ አድርጎ ነበር።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፣ ወደ ዘላቂ የምግብ አጠቃቀም መንገዶች መሸጋገር፣ የከባቢ አየር ጥበቃን ማዕከል ያደረገ የአመራረት ዘዴን መከተል፣ በምግብ ስርዓት ውስጥ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና ለአደጋዎች የማይበገር ጠንካራ የምግብ ስርዓት መገንባት የትኩረት መስኮቹ ናቸው።
እንደ ተመድ ማብራሪያ ከሆነ፤ አምስቱ የተግባር መለኪያዎች ያስፈለጉት በዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ግብ ሁለት ላይ ያለውን ከዓለም ላይ ረሃብን የማጥፋት ውጥን ለማሳካት ነው።
በአካባቢ፣ በሀገር፣ በቀጣና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሄዎችን ማበጀትና የነባር ኢኒሼቲቮች አፈጻጸምን ማላቅ እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
እ.አ.አ በ2024 የወጣው ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሪፖርት ኢትዮጵያ በአምስቱ መለኪያ ያላትን አፈጻጸም አስቀምጧል። በእዚህም ፦
- ለሁሉም ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ ማድረግ
ኢትዮጵያ በምግብ ምርታማነትና ረሃብን በመቀነስ ከፍተኛ ውጤቶች ማስመዝገቧን ሪፖርቱ ያመለክታል።
እ.አ.አ ከ2000 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የጥራጥሬ ምርቷ ከሁለት እጥፍ በላይ ማደጉንና የአንድ ግለሰብ ዓመታዊ የምግብ ፍጆታ ከ288 ኪሎ ግራም ወደ 447 ኪሎ ግራም ማደጉ ተጠቅሷል።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሀገር ደረጃ የከፍተኛ የምግብ እጦት ምጣኔ ከ56 በመቶ ወደ 29 በመቶ ዝቅ ማለቱም ተመላክቷል።
ይሁንና ከምግብ ዋስትና እና ብዝሃ የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም ላይ ፈተናዎች እንዳሉ ሪፖርቱ ይጠቁማል።
በምርታማነትና በእሴት ሰንሰለት ላይ ባሉ ተግዳሮቶች ምክንያት ስጋ እና ወተት የመጠቀም ምጣኔ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ሂደት ውስጥ በማምረት፣ በማቀነባበርና በመሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት ሪፖርቱ ያሳያል።
- ወደ ዘላቂ የምግብ ስርዓት አጠቃቀም መንገዶች ሽግግር ማድረግ
ኢትዮጵያ ብዝሃ የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም ላይ መሻሻል እያሳየች እንደምትገኝ ሪፖርቱ ያመለክታል።
ህጻናት በሚመገቡት ምግብ ውስጥ በርካታ ንጥረ ነገሮችን እንዲያገኙ የማድረግና አዋቂዎች አትክልቶች እና ፍራፍሬዎችን የመጠቀም ሁኔታ ላይም ለውጦች በመታየት ላይ ናቸው።
ይሁንና የዜጎች በተለይም በርካታ ንጥረ ነገሮችን የመጠቀም ምጣኔን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
በቂ ንጥረ ነገር ያለው ምግብን መጠቀም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ቁልፍ ሚና እንዳለው በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ዘላቂ የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም ሽግግርን መፍጠር፣ የስነ ምግብ ትምህርትን ማስፋት እና የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም መመሪያን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ናቸው።
ኢትዮጵያ የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም መመሪያዎችን ብትቀርጽም ግንዛቤ የመፍጠርና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተመላክቷል።
- የከባቢ አየር ጥበቃን ማዕከል ያደረገ የአመራረት ዘዴን መከተል
ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን ከመጨመር ጎን ለጎን የተፈጥሮን ስነ-ምህዳር በመጠበቅ በኩል ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ እየተገበረች በምትገኘው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ እ.አ.አ በ2030 የበካይ ጋዝ መጠንን በ64 በመቶ ለመቀነስ አቅዳ እየሰራች ነው።
ማህበረሰብ ተኮር የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች በተለይም በከፍታ ቦታ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የአካባቢ ጥበቃን የማስፋት ተግባራት ውጤት ተገኝቶባቸዋል።
በደን መልሶ ልማትና የደን ሽፋንን በመጨመር፣ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂን አጠቃቀም እያደገ መምጣት እና የዘር ብዜት ስራዎች በማሳያነት ይጠቀሳሉ።
የአየር ንብረት፣ የአፈር ተስማሚነትና የመሬት አጠቃቀምን መሰረት ባደረገ ሁኔታ መልክዓ ምድራዊ ቀጣናዎችን በመለየት የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ዘላቂ ልምምድ ለመፍጠር እያስቻለ ይገኛል።
የተፈጥሮ ዑደትን በጠበቀ ሁኔታ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፎችን መተግበሯ በሪፖርቱ በመልካምነት ተነስቷል።
የመሬት መራቆት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን በሚፈለገው መጠን አለማደግ፣ የተበታተነ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት እንዲሁም የዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት ተደራሽነት አሁንም ፈተናዎች እንደሆኑና በጉዳዩ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ በምክር ሀሳብ ደረጃ ተቀምጧል።
- በምግብ ስርዓት ውስጥ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረገገጥ
ሪፖርቱ ኢትዮጵያ በዚህኛው መለኪያ በገጠር አካባቢ ያለ ድህነትን በመቀነስና የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ ላይ መሻሻል ማሳየቷን ይገልጻል።
መደበኛ የግብርና እና ግብርና ነክ የንግድ እንቅስቃሴ በጥቅል ሀገራዊ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ ከነጠላ አሃዝ ወደ ባለ ሁለት አሃዝ ማደጉ በስኬት ይጠቀሳል።
የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችና የምግብ ስርጭት አውታሮች መስፋት እንዲሁም በከተሞች ዘመናዊ የሽያጭ ማዕከላት እድገት በመልካምነት ተነስቷል።
በፖሊሲ እና በተቋማዊ መዋቅር ውስጥ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎን የማሳደግ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል።
አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ከገበያ ጋር ማስተሳሰር፣ የእሴት ሰንሰለቱን ማስፋት፣ የቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ተደራሽነት ማደግ፣ የክህሎት ልማት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ማስፋት የተገኙ ውጤቶች ናቸው።
ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶችና አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ለመሬት፣ ብድር፣ ገበያ እና ቴክኖሎጂ ያላቸው ተደራሽነት አሁንም የቤት ስራ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ሪፖርቱ ያስቀምጣል።
የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ፣ ፍትሃዊ የገበያ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የገበያ መረጃ ስርዓትን ማጠናከር፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግና የክህሎት ልማትን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል። ለዚህም የተቀናጀ የተቋማት እና የፋይናንስ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
- ለአደጋዎች የማይበገር ጠንካራ የምግብ ስርዓትን መገንባት
ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓቷ ውስጥ የማይበገር አቅም መገንባት የሚያስችሉ ጠቃሚ እርምጃዎችን እንደወሰደች ሪፖርቱ ያስቀምጣል።
የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን እየተገበረች ትገኛለች።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን በመቀነስ ስትራቴጂ ድርቅ የሚቋቋሙ ሰብሎችን በማምረት፣ ዘላቂ የግብርና አመራረት ዘዴዎችን በመከተልና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመፍጠር ውጤቶች ማግኘቷም ተመላክቷል።
ለድርቅ ተጠቂ በሆኑ ስፍራዎች ለሚኖሩ ዜጎች የምግብና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት ተጋላጭነት ከፍተኛ እንደሆነ ይጠቁምና ለአደጋ አስቀድሞ ምላሽ መስጠት ላይ ለውጦች ቢታዩም የተቀናጀ የምላሽ ስርዓትን ከመከተል አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ የተቀናጀና የባለብዙ ወገን ዘርፎች የአደጋ ስጋት ቅነሳ አስተዳደርን ማጠናከርና የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቷን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባትም ያስቀምጣል።
ሴቶች፣ ህጻናትና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የአደጋ ምላሽ የሚሰጡበትን የአይበገሬነት አቅም መገንባትና የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ማሳደግ በሪፖርቱ ላይ በምክረ ሀሳብነት ቀርቧል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አምስቱን የድርጊት መከታታያ መስኮች ለመተግበር ጠንካራ ቁርጠኝነት ያሳየች ሲሆን በዘርፎቹ ለውጦችን ማምጣት ችላለች።
የምግብ ምርታመነትን በማሳደግ፣ በድህነት ቅነሳና ለምግብ ስርዓት ትራስፎርሜሽን መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን በማከናወን ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገቡንም ያመላክታል።
የንጥረ ምግቦችን ተደራሽነት መጨመር፣ የገበያ ትስስርን ማጠናከር፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እኩልነትን ማረጋገጥ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባትን ጨምሮ የምግብ ስርዓቱ ላይ ያሉ መዋቅራዊ ፈተናዎችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በማምረት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማሳደግ፣ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።
ዘላቂ ኢንቨስትመንት፣ የፖሊሲ መሰናሰንና የባለብዙ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር የማይበገር፣ እኩልነትን የተረጋገጠበት፣ ዘላቂ እና ማንም ወደ ኋላ የማይቀርበት የምግብ ስርዓትን እውን ለማድረግ ወሳኝ ናቸው።
ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አምስቱ የምግብ ስርዓት የድርጊት መከታታያ መስኮች ላይ ሀገራት ያላቸውን አፈጻጸም ይገመግማል።
በቀጣይ መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።