ጋና ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ጋና ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ጋና ደቡብ አፍሪካን በመለያ ምት አሸንፋለች።
ማምሻውን በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቿ ኖንህላህላ ምታናዲ በ45ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ጎል ደቡብ አፍሪካን መሪ አድርጎ ነበር።
የደቡብ አፍሪካዋ ግብ ጠባቂ አንዲሌ ድላማኒ በ65ኛው ደቂቃ በራሷ መረብ ላይ ያስቆጠረችው ግብ ጋናን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው በመደበኛ 90 ደቂቃ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቷል።
በዚህም ጋና 4 ለ 3 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካ አራተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሯን አጠናቃለች።
ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ደቡብ አፍሪካ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ እ.አ.አ በ2016 በካሜሮን አስተናጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ባደረጉት ጨዋታ ጋና 1 ለ 0 ማሸነፏ አይዘነጋም።
የ13ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ መርሃ ግብር በአዘጋጇ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ መካከል ነገ ይደረጋል።