ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲ በጨረፍታ

የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ በአንድ ሀገር ውስጥ ምርታማ የሰው ኃይል ለመፍጠር የሚወጣው ሚና አይተኬ ነው።

ረጅም እድሜ እና ጤናማ ህይወት ለመኖር፣ የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የመፍጠርና የፈጠራ ብቃትን የማሳደግ ፋይዳም አለው።

የሚያስገኘው ጥቅም ተዳምሮ የሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ እድገትን በማፈጠን ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ያስችላል።

ይሄ ግን እውን የሚሆነው በሁሉም የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ጤናማ ህይወት ሲኖሩ፣ ስለ ተመጣጠነ ምግብ ጠቃሜታ በቂ ግንዛቤ ሲያገኙ፣ የምግብ አጠቃቀም የተሻሉ መንገዶችን መከተልና የምግብ ደህንነትና ጥራት በሁሉም የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ማረጋገጥ ሲቻል ነው።

የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ብክነትን ማስወገድ፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ስትራቴጂ መቅረጽ እና አይበገሬነትን መገንባት ያስፈልጋል።


 

የኢትዮጵያ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲም በሀገሪቱ ለሁሉም ዜጋ ያልተቋረጠ ደህንነቱ የተረጋገጠና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን የማረጋገጥ አላማ አንግቦ ከሰባት ዓመት በፊት ይፋ ሆኗል።

ፖሊሲው የምግብ ተደራሽነት፣ ለምርታማነት፣ ለጤና እና ዘላቂ ልማት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያስቀምጣል።

መቀንጨር እና መቀጨጭ ላይ ከፍተኛ ለውጦች ቢታዩም የምግብ ምርታማነት እያደገ ከመጣው ህዝብ አንጻር በሚፈለገው መጠን አለመጨመር፣ የስርዓተ ምግብ መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለመሟላትና የምግብ ደህንነት እና ተደራሽነት ላይ ያሉ ክፍተቶች፣ በቂ ያልሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የንጽህና አጠባበቅ የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ለመፍታት መንግስት በሕግ በተደገፈ አሰራርና ሁሉን አሳታፊ አካሄድን እንደሚከተል በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ምግብ ሰብዓዊ መብት ነው የሚለው ይህ ፖሊሲ የከፋ የመቀንጨር ችግርን የማስወገድና በትውልዶች ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ የመከላከል ውጥን አለው።


 

ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልጋቸውን የተመጣጠነ ምግብ ና የምግብ ግብዓቶች እንዲያገኙ ማድረግ፣ የኑሮ ሁኔታን ማሻሻልና ምርታማነትን ማሳደግ  የፖሊሲው ራዕዮች ናቸው።

የተቀናጀ የስርዓተ ምግብ ምላሽ በመስጠት በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ጥራት  ያለው፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ብዝሃ ፍላጎትን የሚመልሱ ምግቦችን እንዲያገኙ በማድረግ ጤና እና ደህንነት የመጠበቅ ግብ እንዳለው ተጠቅሷል።

ሁሉን አቀፍነት ዋነኛ መገለጫው የሆነው የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲ ከኢትዮጵያ ሕገ- መንግስት እና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የተጣጣመ ሲሆን የመንግሥት የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ አንዱ አካል ነው።

ፖሊሲው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን)፣ የስነ ህዝብ ለውጦችና የከተሜነት መስፋፋት የምግብ ስርዓቱ አበይት ፈተናዎች መሆናቸውን ይገልጻል።

ለችግሮቹ መፍትሄ በማበጀት በሁሉም ደረጃ ዘላቂ የምግብ ተደራሽነት፣ ደህንነትና አጠቀቃምን በማረጋገጥ ዜጎች ረጅም እና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ያስቀምጣል።  

የምግብ ተደራሽነትና አጠቃቀም፣ የምግብ ደህንነት፣ የድህረ ምርት ብክነት አስተዳደር፣ የስርዓተ ምግብ ዑደትን በሁሉም የእድሜ ክልል ለውጦች ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ፣ ተግባቦትና የአስተዳደር መዋቅርን ማጠናከር የፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

የፖሊሲው ትግበራና አካሄድ የህይወት ዑደት ደረጃዎችን ያማከለ፣ ከእርሻ እስከ ጉርሻ የሚለውን ሁለንተናዊ መንገድ የሚከተልና ለባለድርሻ አካላት ትብብር ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።


 

የስርዓተ ምግብ ውጤታማነትን የሚያረጋግጡ በቀጥታና ተዘዋዋሪ መንገድ የረጅም ጊዜ ውጤት የሚያስገኙ ስትራቴጂዎችን በውስጡ ይዟል።

ከስትራቴጂው መካከል እ.አ.አ 2021 የተቀረጸው የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ይገኝበታል።

ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ ስርዓተ ምግብ ከትምህርት ጋር በማስተሳሰርና ሴቶችን በማብቃት የሰው ኃይል ልማት ስራው አንኳር የትኩረት አጀንዳዎች መሆናቸው ተመላከቷል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላትን ማጠናከር፣ የልህቀት ማዕከላትን ማቋቋምና ተቋማት በምግብ ደህንነት ላይ ያላቸውን የክትትልና የቁጥጥር አቅም ማሳደግ የእቅም ግንባታ ስራው አካል ናቸው።

ለምግብ እና ስርዓተ ምግብ ስራዎች የፋይናንስ ምንጮች መንግስት፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ማህበረሰቦችና የመንግስት የግል አጋርነት መሆናቸውን የሚገልጸው ፖሊሲው ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦትን ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረት እንደሆነ ያስቀምጣል።

ፖሊሲው ለስርዓተ ጾታ እኩልነት ትኩረት በመስጠት ሴቶች በስርዓተ ምግብና በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲያድግ ድጋፍ ይሰጣል።

መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍና ማህበረሰቦች ቁልፍ የስርዓተ ምግብ ተዋንያን እንደሆኑ በፖሊሲው ላይ ተመላክቷል።

መንግስት በአመራር  ሰጪነት፣ የህግ ማዕቀፎች የማዘጋጀት እና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለፖሊሲው የሚያስፈልግ ሀብት ከተለያዩ ቋቶች የማሰባሰብ ድርሻ አላቸው።

የግሉ ዘርፍ በምግብ ምርትና ማቀነባበር ውስጥ ዘላቂ እና ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድን የመከተል ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ዜጎች በምግብ እና ስነ ምግብ ኢኒሼቲቮች የተሳትፎ እና የባለቤትነት ሚናን ይወጣሉ።

በፖሊሲው የተቀናጀ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት የተዘረጋ ሲሆን በእያንዳንዱ ስራ ውስጥ ቁልፍ መለኪያዎች ተቀምጠዋል።

የክትትል እና ቁጥጥር ስርዓቱ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ተቋማት ያለውን ይሸፍናል። የቅኝት እና የዳታ አስተዳደር ስራንም ያካትታል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የምግብና የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ ሁሉን አቀፍ፣ የዜጎችን መብት ያማከለ እና የባለ ብዙ ወገን ትብብር አካሄድን የሚከተል ነው።

ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ብዝሃነት ያለውና የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ በፖሊሲው ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች በልዩነት ድጋፍ ያደርጋል።

የፖሊሲው የመጨረሻ መዳረሻ በምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።

ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ የሀገራትን ብሄራዊ የስርዓተ ምግብ ፖለሲዎች የሚገመግም ሲሆን የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ሁነት በስርዓተ ምግብ እያከናወነች ያለውን ስራ በተሞክሮነት የምታቀርብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም