ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በጋራ የመልማትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ የዕድገት ጥያቄ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በጋራ የመልማትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የሰጥቶ መቀበል መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰኔ ወር መጨረሻ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የሰላምና የልማት ትብብር ማስቀጠል ፍላጎት አላት ማለታቸው ይታወሳል።

ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጎረቤት ሀገራት በጎ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ማለታቸውም እንዲሁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የባህር በር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና በፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ውስጥ የምትገኝ ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ ለዚህም የባህር በር ባለቤትነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ተከትሎ የወጪና ገቢ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በጋራ የማደግና የመልማት መርህን በመከተል የባህር በር ፍላጎትን ሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በባህር በር ላይ ያላትን አቋምና እየሄደችበት ያለውን መንገድ ለዓለም ሀገራት በማስረዳት ተቀባይነት እያገኘች መምጣቱንም ጠቁመዋል።

የባህር በር ጉዳይን በአጀንዳነት ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ የማራመድ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ዲና በአጽንኦት አንስተዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ የባህር በር አጀንዳ ወሳኝና የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሌላውን የመጉዳት ሳይሆን የመልማት ፍላጎቷን ለማሳካት የባህር በር ጥያቄ በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ የባህር በር ጉዳይን የጥናትና ምርምር ማዕከል አጀንዳ በማድረግ ስትራቴጂዎችን ለማውጣትና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር በጋራ የመልማት ፍላጎቷን ለማስረጽ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮችን መዘጋጀቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም