ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የሚደረጉ ጥናት እና ምርምሮች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያስቻሉ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 18/2017(ኢዜአ)፡-በግብርናው ዘርፍ የሚደረጉ ጥናት እና ምርምሮች የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያስቻሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢንስቲትዩት  በግብርናው እሴት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በጥናትና ምርምር መለየት፣ ለማነቆዎቹ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዘርፉ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ሃሳቦች ገቢራዊ እንዲሆኑ በማስቻል ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል። 

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው በሜካናይዜዥን እንዲያመርቱ፣ ግብዓት በቀላሉ እንዲያገኙና  የተመረተውን ምርት በጋራ ሰብስበው መሸጥ እንዲችሉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል። 

ኢንስቲትዩት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ የልማት አቅጣጫን ለመቀየሰ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አርሶ አደሮች  ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የግብርና ኬሚካል እንዲያገኙ እንዲሁም ስልጠና ማግኘት የሚችሉበት የአንድ መስኮት አገልግሎት እየተስፋፋ ይገኛሉ።  


 

እንዲሁም  ትራክተር ፣ ኮምባይነር፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች ፣ መጋዘኖች ፣ የዘር ማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽኖች ለኅብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

በተከናወኑ ተግባራት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን አንስተው በተለይ በኩታ ገጠም ተደራጅተው የሚያርሱ አርሶ አደሮች 30 ከመቶ የምርት ጭማሪ ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶ አደሮቹ የገቢ መጠን ማደግ መቻሉን አመልክተዋል። 


 

በቀጣይ በኩታ ገጠም የሚታረሱ አካባቢዎች ላይ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች መገንባት፣ የተመረተው ምርት ላይ እሴት መጨመርና ለውጥ ያመጡ አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ለሁሉም ክልሎች መዘጋጀቱንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም