በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ።

ጨዋታው በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ጋና በግማሽ ፍጻሜው በአዘጋጇ ሞሮኮ በመለያ ምት 4 ለ 2 የተሸነፈች ሲሆን የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ደቡብ አፍሪካ በናይጄሪያ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዳለች።

ሁለቱ ሀገራት በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት አንድ ላይ የነበሩ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ጀርሜን ሴፖሴንዌ በጨዋታ እና ሊንዳ ሞትሃሎ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ግቦች ደቡብ አፍሪካ 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ቡድኖች በአጠቃላይ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው ጋና ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ደቡብ አፍሪካ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷታል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ከዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ከዚህ ቀደም በአህጉራዊው መድረክ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።


 

ናምቢያ እ.አ.አ በ2014 ባሰናዳችው ዘጠነኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ2016 በካሜሮን አስተናጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ባደረጉት ጨዋታ ጋና 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት መጫወታቸው ግጥምጥሞሹን የተለየ አድርጎታል።

ደቡብ አፍሪካ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ኳስን ይዞ የመጫወት ዘይቤ እና የመሐል ክፍል የመቆጣጠር ብቃት እንዲሁም የታክቲክ ተገዢነቱ ጠንካራ መገለጫው እንደሆነ  ለመመልከት ተችሏል።

የአካል ብቃት ላይ ያመዘነ አጨዋወት፣ የረጅም ኳስ አጠቀቃም እና ፈጣን መልሶ ማጥቃት  የጋና ብሄራዊ ቡድን መለያ ነው።

ደቡብ አፍሪካ ጨዋታውን በጠባብ የግብ ልዩነት ታሸንፋለች የሚሉ ግምቶች እየወጡ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም