ቀጥታ፡

ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለሰላም እና ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበት በጋራ እንሰራለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 18/2017(ኢዜአ)፡-ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለሰላም እና ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበት በጋራ እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባወጡት የጋራ ቃል ኪዳን ገለጹ።

ሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት "ሠላምን ለማፅናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገራዊ ኮንፍረንስ ላለፉት ሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሀገራዊ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም አውድ እና የሀገርን ሰላም ለማጽናት ያላቸው ሚና ላይ በዝርዝር መክረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላማዊ ፖለቲካ ትግል ተምሳሌት መሆናችንን በመገንዘብ፣ ለቆምንለት የህብረተሰብ ክፍል፣ ሀገር እና ትውልድ ሰላም እንዲጸና እንደፖለቲካ መሪነታችን ሃላፊነትን እንወጣለን ብለዋል።


 

ሠላም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ባለ 7 አንቀጽ የቃል ኪዳን ነጥቦችን  አውጥተዋል።

በጋራ ቃል ኪዳናቸውም ሠላማዊና የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ በመከተል የፖለቲካ ዓላማቸውን በዲሞክራሲያዊ፣ በሕግና በስርዓት እንደሚያከናውኑ አረጋግጠዋል።

ለዲሞክራሲ ተቋማትና እሴቶች መከበር እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።


 

ለአካታችነት፣ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለብሄራዊ ጥቅም መጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ለዲሞክራሲያዊ መልካም አስተዳደር መስፈን በአጀንዳ፣ በፖሊሲ፣ በችሎታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመገንባት የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍላጎት መኖርን እንደ ጤናማ ዲሞክራሲ ምልክት እንደሚቀበሉም ገልጸዋል።

ለብሄራዊ ጥቅም እና ለዲሞክራሲ ስርዓት መጽናት እንደሚሰሩ እና በዜጎች ክብር እና በሀገራችን ዕጣ ፋንታ ላይ በጋራ በመቆም የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማጽናት እንደሚተጉ አንስተዋል።

የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን (ዲክላሬሽን) ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:- 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን በማስፈንና በማጽናት የሚኖረን ሚና ላይ የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን( ዲክላሬሽን)

ቀን ሀምሌ 17/2017 ዓ.ም

ቢሾፍቱ

ሰላምን በማስፈንና በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ የሚመክር የሠላም ኮንፍረንስ መድረክ አካሂደናል፡፡

መድረኩ በጋራ ም/ቤት ዕቅድ መሠረት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ የቆየ ሲሆን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የም/ቤት ከኢፌድሪ ሠላም ሚኒስተር ጋር በመሆን ዕዉን ማድረግ ተችሏል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን ማስፈንና ማጽናት በሚል መሪ ሃሳብ የሚመክር ሀገራዊ መድረክ በመዘጋጀቱ ምስጋናችን የላቀ ነዉ፡፡ በመድረኩ ሀገራዊ የሠላም አዉድና እና አለማቀፍ ገጽታዉን በንድፈ ሃሳብና በተለያዩ ተሞክሮዎች ለሀገራችን ሠላም መስፈንና ማጽናት ባለዉ ፋይዳ በምሁራን በቀረቡ የዉይይት ሰነዶች ላይ ተመስርተን የሠላምን ምንነትና መገለጫዎችን፣ በሰላም ላይ ቀጠናዊ እና ዓለማዊ ሁኔታ የሚኖረዉን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሰላም ተዋኒያን ማንነት እና ሃላፊነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና እና  በመጨረሻም የሀገራችን የሰላም ችግር መነሻዎችና የመፍትሄ አቅጣጫ ላይ በጥልቀት ተወይተናል፡፡ ይህም እንዲሳካ በዉይይት ቡድን በመከፋፈል በዝርዝር ከተመለከትን በሗላ በዉይይት ነጥቦች ዙሪያ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመያዝ እድል አግኝተናል፡፡ በዚህም፡-  

ሠላም የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን፣

እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ተምሳሌት መሆናችንን በመገንዘብ፣ 

ለቆምንለት የህብረተሰብ ክፍል፣ሃገር እና ትዉልድ ሰላም እንዲጸና 

     እንደፖለቲካዊ መሪዎች ሃላፊነት መወጣት እንዳለብን በማመን፣

ሠላም ለዲሞክራሲ ስርኣት ግንባታ ያለዉን የማይተካ ሚና 

 በመገንዘብ፣

ይህን እምነታችንን በዚህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ ይፋ ስናደረግ ለተግባራዊነቱ የባለድርሻ አካላትም ሚናቸዉን አንዲዎጡ ባለ 7 አንቀጽ የቃል ኪዳን ነጥቦች ላይ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አንቀጽ 1: ሠላማዊና የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ የመከተል ቃል ኪዳን

    1.1.    የፖለቲካ ዓላማችንን በዲሞክራሲያዊ እና በሕግና በስርዓት 

          እናከናወናለን።

    1.2.    ጸጥታን በማደፍረስ፣ የስም ማጥፋትና ጥላቻ እንዲሁም ለሰዉ 

          ህይዎትና ንብርት መጥፋት ምክንያት ባላመሆን ለሰላም እንተጋለን።

አንቀጽ 2: ለዲሞክራሲ ተቋማትና እሴቶች ክብር የመስጠት ቃል ኪዳን

    2.1.    ሕግና ሥርዓት፣ የህዝብ ውሳኔ ወሳኝነት፣ የምርጫ ሂደቶችና ዉጤት እንዲከበሩ።

    2.2    በውሳኔዎች ላይ ልዩነት ቢኖር እንኳ ህጋዊነትን በማክበር አቋማችንን ማራመድ፡፡

አንቀጽ 3: ለአካታችነት፣ ለሀገራዊ መግባባትና ብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም 

          ኪዳን 

ያሉንን ልዩነቶችን ክብርና ልዩ ትኩረት በመስጠት ለህብረብሄራዊነት 

           እሳቤ ግንባታ ለመስራት ተስማምተናል።

የወጣቶች፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንድያድግ በትኩረት እንሰራለን፡፡

ለብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም የፖለቲካ ባህል አንገነባለን፡፡ 

አንቀጽ 4: ለዲሞክራሲያዊ መልካም አስተዳደር መስፈን የመስራት ቃል ኪዳን፡፡

በአጀንዳ፣ በፖሊሲ፣ በችሎታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት 

          ለመገንባት እንሰራለን።

የተለያዩ የፖለቲካ አስተሰሰብና ፍላጎት መኖር እንደ ጤናማ ዲሞክራሲ 

          ምልክት እንቀበላለን።

አንቀጽ 5: የግጭት አያያዝ  እና የሰላም ግንባታ ዉጤታማነት የመስራት ቃል 

         ኪዳን፡፡

በየፓርቲዎቻችን ውስጥና በሌሎች ፓርቲዎች መካከል ለግጭቶች 

          ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሥርዓቶችን እንገነባለን።

በማህበረሰብ፣ በአካዳሚያ፣ በተለያዩ መድረኮች እና ከፖለቲካ 

          አመራሮች ጋር በሚካሄዱ የሰላም ውይይቶች በአጋርነት እንሳተፋለን።

አንቀጽ 6: የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የመዳበር ቃል ኪዳን፡፡

በመንግስት እንዲሁም በፓርቲያችን ውስጥ ግልጽነት፣ የሐሳብ ነጻነትና    

          መተማመን እንዲጎለብት እንተጋለን።

የህዝብ ተሳትፎ የሚገድብ ሥራ እና ተቋማዊነት የሚጎዳ የፖለቲካ 

          አካሄድ በጋራ አንታገላለን፡፡

አንቀጽ 7: ለብሄራዊ ጥቅም እና ለዲሞክራሲ ስርዓት የመጽናት ቃል ኪዳን፡፡

በሰላም፣ በዉጫዊ ችግሮች፣ በብሄራዊ ምርጫ እና በመንግሥት 

          ልማት አካል እንደአንድ አካል እንሰራለን።

በኢትዮጵያ የዜጎችና ህዝቦች ክብር እና በሀገራች የጋራ ዕጣ ፋንታችን 

          ላይ በጋራ በመቆም ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማጽናት እንሰራለን።

መደምደሚያ መግለጫ

ይህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ፣ እኛ እንደፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከፍተኛ የሰላም መሪነትን፣ ማህበራዊ ሀላፊነትን እና ከሀገራዊ የጋራ ፍላጎትና ጥቅም በመነሳት ለመስራት ካለን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። ከዛሬ ጀምሮ ፖለቲካዊ ልዩነታችን አንደተጠበቀ ሆኖ ለአገርና ለህዝቡ ጥቅም ሲባል በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት በትጋት ለመስራት እንተጋለን።

ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አዉድ ዉጪ ያላችሁ የፖለቲካ ሃይሎችና የታጠቁ ቡድኖች ልዩነቶችን በሠላማዊ ጠረጴዛ ዙሪያ አንዲፈታ ሚናችሁን አንዲትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ለስኬታማነቱም ሚናችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡ 

በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት የሚያግዙ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከሚመለከታቸዉና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ተስማምተናል፡፡

                   

ሰላም የሁሉ መሰረት ነዉ!!!

ሃምሌ 17/2017 ዓ.ም

ቢሾፍቱ

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም