ቀጥታ፡

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን በማጠናከር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ያስፈልጋል-የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 17/ 2017 (ኢዜአ)፦ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን በማጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በማዳበር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የፖለቲካ ልሂቃን ሚናቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ያስተናገደቻቸው በርካታ የእርስ በእርስ ግጭቶች የዜጎቿን ህይወት ነጥቅዋል፤ በርካታ ንብረትን አውድመዋል።

ከዚህም ባለፈ ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት በማጋለጥ የልማት ግቦቿን እንዳታሳካ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን ነው ያነሱት።

በአገሪቷ ሰፊ ሀብት እና በርካታ የአብሮነት እሴቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ ሆኖም ፖለቲካዊ ግብን በኃይል ለማሳካት የሚደረጉ ሙከራዎች ወደኋላ አስቀርተውናል ነው ያሉት።

አለመግባባት የሚፈጥር የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ እንዲሁም የእኔ አውቅልሃለሁ አስተሳሰብ ግጭትን ከመውለድ ያለፈ ሚና እንደሌለውም አስረድተዋል።

የመጣንበት መንገድ አያዋጣም ያሉት ሰብሳቢው፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረግ ጥረት የሚያሳካው ግብ እንደሌለም ተናግረዋል።

በመሆኑም ካለፉት ግጭቶች በመማር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገርን በጋራ ለመገንባት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን እና የውይይት ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በሰላም ጉዳይ ላይ እንደሀገር አብሮ መስራት፣ በሀሳብ ልዕልና የሚገዛ የፖለቲካ አውድን መፍጠርና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሟላት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የያዙት መንገድ እነርሱን ብቻ ሳይሆን ሀገርና ህዝብን የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ግጭት ሰላማዊ የሆነውን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምህዳር እንደሚያናጋ ገልጸው፤ለዚህ ደግሞ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን በላይ ምስክር የለም ነው ያሉት።

በሀሳብ መወያየትና ችግሮችን መፍታት ለሀገር ግንባታ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢው፤ ነፍጥ አውርዶ ወደ ጠረጴዛ ውይይት መምጣት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፖለቲካ ልሂቃንም የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለሁሉም ነገር መሰረት ለሆነው ሰላም የትኛውንም ዋጋ መክፈል የግድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም