የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ለዘላቂ የዱር እንስሳትና እጽዋት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ለዘላቂ የዱር እንስሳትና እጽዋት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
ባሌ ሮቤ፤ሐምሌ 17/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ከመቀነስ ባሻገር ለዘላቂ የዱር እንስሳትና እጽዋት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በዚህም የተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ዐሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለሥልጣን አመራሮችና ሰራተኞች በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ከዘላቂ የፓርኮችና ሌሎች የተፈጥሮ ኃብት የጥበቃ ዘርፍ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነው።
ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የደን ሽፋንን በማሳደግ ለዱር አራዊት ምግብና መጠለያ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመርኃ ግብሩ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች የፓርኮችና ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች ይዞታ እየተሻሻለና የዱር አራዊት የአደጋ ተጋላጭነትም እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል።
ከተፈጥሮ ኃብት የጥበቃ ሥራ ስፋትና ውስብስብነት የተነሳ በቀጣይም ማህበረሰቡን ያሳተፈ ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በመርሐ ግብሩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው ሀገር በቀል ዕፅዋት መተከላቸውን ጠቁመው ችግኞቹን እስከ ጽድቀታቸው ድረስ መንከባከብ ከሁሉም የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የመትከል ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የችግኝ ተከላው በተለይ በብዝሐ ህይወት በበለጸገው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ አካባቢዎች መካሄዱ በፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፉ የተቋሙ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የዓለም ቅርስ በሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል ።
ችግኞቹ ጸድቀው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።
በመርሐግብሩ ከተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቋሚ ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደጋ አጋዘንና ቀይ ቀበሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር አራዊት፣ እጽዋትና የማራኪ መልክዓ ምድር መገኛ ነው።