የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ከ43 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ከ43 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 17/2017(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል ከ43 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።
የክልሉ ምክር ቤት በጀቱን ያጸደቀው በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ በሚገኘው 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 4ኛው መደበኛ ጉባኤ ነው።
በክልሉ ምክር ቤት የፋይናንስና በጀት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ታመነ ገብሬ የተያዘውን በጀት ለወሳኝ ተቋማት እና እንደሀገር በኢኒሼቲቭ ለሚሰሩ ሥራዎች በአግባቡ እንዲውል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ታመነ ገለጻ በጀቱ በዋናነት ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለድህነት ቅነሳ ሥራዎች፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውልም ተናግረዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በሰጡት ማብራሪያ የበጀቱ ምንጭ የክልሉ የውስጥ ገቢ፣ ከፌደራል መንግስት የሚሰጥ ድጎማ እና ሌሎች የገቢ ምንጮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮ በጀት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ እድገት እንዳለው ጠቅሰው፣ ከአጠቃላይ በጀቱ 23 ቢሊዮን 724 ሚሊዮን 463 ብር በክልሉ የውስጥ ገቢ የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል።
በራስ አቅም የሚሰበሰብ ገቢ እያደገ በመሆኑ ሁሉም መዋቅሮች የገቢ አሰባሰብ አቅማቸውን ለማሳደግ፣ በጀታቸውን በአግባቡ ለማስተዳደርና ግልጽነት መፍጠር ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ኃላፊዋ አሳስበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የበጀት ረቂቅ ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተው ከተወያዩ በኋላ በጀቱን አጽድቀዋል።