ስፔን ጀርመንን በመርታት ለፍጻሜ ደርሳለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር  ስፔን ጀርመንን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።

ማምሻውን በሌትዝግሩንድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በመደበኛ 90 ደቂቃ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሯል።

በጭማሪ ሰዓት የሁለት ጊዜ የባለንዶር አሸናፊዋ አይታና ቦንማቲ በ113ኛው ደቂቃ በድንቅ አጨራረስ ያስቆጠረችው ግብ ስፔንን  ወደ ፍጻሜው አድርሷል።

ለጎሉ መቆጠር የጀርመን ተከላካዮች  ትኩረት ማጣት እና የጀርመን ግብ ጠባቂ አና-ፓትሪክ በርገር የቦታ አጠባበቅ ክፍተት አስተዋጽኦ አድርጓል።

ስፔን በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድል በመፍጠር የተሻለ ነበረች።

የጀርመን ጠንካራ ተከላካይ መስመር እና አይበገሬ መንፈስ አድናቆት የሚቸረው ነው።

የአውሮፓ ኃያላኑ ፍልሚያ በስፔን የበላይነት ተጠናቋል። ቡድኑ ለሴቶች አውሮፓ ዋንጫ ሲያልፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የወቅቱ የሴቶች ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስፔን በፍጻሜው ከወቅቱ የሴቶች አውሮፓ አሸናፊ እንግሊዝ ጋር የፊታችን እሁድ ሐምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

የስምንት ጊዜ የሴቶች አውሮፓ አሸናፊ ጀርመን ለዘጠነኛ ጊዜ የማንሳት ህልሟ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ተገቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም