በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናትና ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ የምናበረክተውን አስተዋፅኦ እናጠናክራለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናትና ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ የምናበረክተውን አስተዋፅኦ እናጠናክራለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናትና ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ "ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ተካሄዷል።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ታድመዋል።
በዚህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንደገለፁት ሰላም ለአገር ልማትና ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላምን ለማፅናትና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ሊሰሩ ይገባል።
የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ እንዳሉት ሰላም ለልማትና ዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ካለው አስተዋፅኦ በተጨማሪ የመንግስትና ህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው።
በሀገር የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ወሳኝ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሰላም ለሀገርና ህዝብ እንዲሁም ለምናልመው ብልፅግና ወሳኝ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለማፅናት እንሰራለንም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የሐረሪና የድሬዳዋ የዞን ምክር ቤት ሰብሳቢ ዮናስ በትሩ መንግስት ስለሰላም የሚመክር መድረክ ማዘጋጀቱ አዲስ ልምምድና ሊዳብር የሚገባው ነው ብለዋል።
ማንኛውም ፓርቲ አባላቱን ስለሰላም ማስገንዘብና በሰላም ዙሪያ ፅኑ አቋም እንዲኖራቸው ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የወለኔ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ፈይሰል አብድላዚዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የመንግስት አካላት ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ሰላምን ለማፅናት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመንግስት በኩል የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉም የፓርቲ አመራሮቹ ተናግረዋል።