የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገረ መንግስት ግንባታ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገረ መንግስት ግንባታ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገረ መንግስት ግንባታ የጀመሩትን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ "ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ታድመዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የብዙ አካላት ድምር ውጤት ዘለቂ ሰላምን ያጸናል።
በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት እንዳለ ሆኖ ለጠንካራ ሀገር ግንባታ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰላምና ልማትን ከሀገር ነባራዊ አውድ ጋር በመቃኘት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የመድብለ ፓርቲ ልምምድ በአግባቡ በማስተዳደር ለሀገር እድገትና ዘለቂ ሰላም አበርክቶ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገረ መንግስት ግንባታ የጀመሩትን ሰላማዊ ትግል በማጠናከር በፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት በአገራዊ ስሜት ሊሳተፉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በሰለጠነ መንገድ በንግግር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች መድረኮች መፈጠራቸውን አስታውሰዋል።
እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ ሀገርን በማስቀደም አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት በተጀመሩ ሂደቶች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል።
የሰላም ሚኒስቴር የፖለቲካ ሊሒቃንን፣ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና ሌሎች ተዋንያን በሀገር ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ የማስተባበር ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።