ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥ ለማጎልበት አርዓያ መሆን አለበት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ ጋር የሚራመድ ብቻ ሳይሆን የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥና የመፈፀም አቅም ለማጎልበት አርዓያ መሆን እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንስቲትዩቱን የቢሾፍቱ ማሰልጠኛ ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የስልጠና ክፍሎችንና የስልጠና ማዕከሉን የሥራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ ለረጅም ዓመታት የመንግስትና የግል ዘርፉን በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ሙያተኞችን አቅም በመገንባት እና በማብቃት ለበርካታ ዓመታት ጉልህ አሻራውን ማሳረፉን ገልጸዋል።

የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደርን ለማሻሻል የተጀመረውን ሪፎርም በመደገፍም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።

የቢሾፍቱ ማሰልጠኛ ማዕከልም ለበርካታ ተቋማት ስልጠና በመስጠት፣ በማማከር እና በዘርፉ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኝ፣ ውብ የአረንጓዴ ገጽታና ሰፊ ግቢ እንዳለው ተመልክተናል ነው ያሉት።

የኢንስቲትዩቱ ማሰልጠኛ ማዕከል ከብልፅግና ጉዟችን ጋር አብሮ የሚራመድ ብቻ ሳይሆን የመንግስትን እና የግል ዘርፉን ተቋማዊ ለውጥ እና የመፈፀም አቅም ለማጎልበት አርዓያ መሆን አለበት ብለዋል።


 

ሀገራዊ መሻትን ያገናዘቡ፣ በሰልጣኞች ዘንድ እውቀትን፣ ሀሴትን እና የለውጥ ቁጭትን የሚፈጥሩ ምቹ የማሰልጠኛ፣ የሰልጣኞች ማደሪያና የመዝናኛ ክፍሎችን እንዲገነባም አሳስበዋል።

የፌዴራል መንግሥት የሥልጠና ማዕከሉን ለማዘመን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም