ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የዛምቢያ እና የቱኒዝያ አምባሳደሮች አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ካሸምቤ ሳካላን እና የቱኒዝያ አምባሳደር አብዱልሃሚድ ግሃሪቢን አሰናበቱ።

ፕሬዚዳንት ታዬ አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

በሌላ በኩል ተሰናባች አምባሳደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነቷን በሚመጥን መልኩ ሁሉን አቀፍ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን በቆይታቸው መገንዘባችውን ተናግረዋል።


 

ፕሬዚዳንት ታዬ ከሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ያደረጉትን ውይይት የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከዛምቢያ እና ቱኒዝያ ጋር ያላት ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።

በዚህም ፕሬዚዳንቱ የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች በቆይታቸው ግንኙነታቸው እየተጠናከረ አንዲመጣ ላደረጉት አስተዋጽኦ ማመስገናቸውን አምባሳደሩ አውስተዋል።

ኢትየጵያ በተለይም ከዛምቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት ያብራሩት አምባሳደር ዘሪሁን፤ በታሪክ ተቋርጦ የማያውቅና ከነጻነት ትግል ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ማንሳታቸውን ተናገረዋል።

የዛምቢያዋ ተሰናባች አምባሳደር ሳካላን የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት በቆይታቸው ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ተገልጿል።

በተመሳሳይ የቱኒዝያው አምባሳደር አብዱልሃሚድ ግሃሪቢን በአምስት አመት የኢትዮጵያ ቆይታቸው የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር ጥረት ማድረጋቸውን አምባሳደር ዘሪሁን ገልጸዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ እና በቱኒዝያ መካከል ያለው የንግድ ትስስር እንዲጠናከርና የባለብዙ ወገን መድረኮች እንዲፈጠሩ ትልቅ ጥረትም አድርገዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ አምባሳደር ሮዝ ካሸምቤ ሳካላን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ሁሉን አቀፍ ትብብር እያደገ መምጣቱን አውስተዋል።

ተሰናባቿ አምባሳደር ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ ጋር የነበራቸው ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸው፤ ሁለቱ ሀገራት በፓን አፍሪካኒዝም እና በሌሎች ዘርፎች ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቱኒዝያ አምባሳደር አብዱልሃሚድ ግሃሪቢን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ልማት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።

ይህንኑ አድናቆታቸውንም ለፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ እንደገለጹላቸው አስታውሰዋል።

በተለይም አሁን በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ላለው የልማት ስኬት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል አመራርን አምባሳደሩ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም