ፌደራል ፖሊስ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ የልማት ዕቅዶች በውጤታማነት እንዲተገበሩ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ፌደራል ፖሊስ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ የልማት ዕቅዶች በውጤታማነት እንዲተገበሩ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ በሀገር ደረጃ የተያዙ የልማት ዕቅዶች በውጤታማነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2018 በጀት ዓመት ሀገራዊ ዕቅድና በተቋሙ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ አመርቂ ድሎችን ማስመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉትም፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ጠንካራ ስራዎችን በመሥራት የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሀገር ደረጃ የተሻለ ሰላም እና ደኅንነት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቁመው ይህንንም ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እውን ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ፣ በጸጥታ፣ በዲጂታል እና በሌሎችም ዘርፎች አመርቂ ድሎች ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ለድሎቹ መገኘትም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ስራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ሀገር የያዘቻቸው የልማት ዕቅዶች በውጤታማነት እንዲከናወኑ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጣም ጠቁመዋል።
በኮሚሽኑ የማዕከላዊ ፖሊስ ኢንተለጀንስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮለ ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መሥራቱን ተናግረዋል፡፡
የወንጀል መከላከልና ምርመራ አቅሙን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ የወንጀል መከላከል የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ እና መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
የወንጀል ምረመራ ስራውም የማስረጃ እና ኢንተለጀንስ መር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከፍተኛ ስራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮለ አያይዘውም ፌደራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ አቅሙን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሥራቱን ጠቁመው የፎረንሲክ ዲጂታል ኢንስቲትዩት ማቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡
የዘረ መል ምርመራ በኢትዮጵያ እንዲኖር ማድረግ ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በኮሚሽኑ የሰው ሃብት ስራ አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደርቤ ገቢሳ በበኩላቸው ፌደራል ፖሊስ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ እንዲሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎንም በልማት ስራዎችም ላይ እየተሳተፈ ትላልቅ ሀገራዊ ለውጥ ባስገኙ ስራዎች ውስጥ አሻራ ማኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ባሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት አንዱ የመሆን ራዕይን አንግቦ እየሰራ ነው፡፡