ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ቁርጠኛ ናት ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ከልኡክ ቡድናቸው ጋር በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ጄኔቫ የሚገኙት ሚኒስትር ዴኤታው ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዋላ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።


 

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ቁርጠኛ መሆንዋንና እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶችን እንዲሁም ለ6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ያላትን ዝግጁነት አብራርተዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያን የአባልነት ድርድር ለማጠናቀቅ በሁሉም ደረጃ ባሉ የመንግስት አካላት ያለው ቁርጠኝነት አስተማማኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርድሩን በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ይህንኑ ፍጥነትና ትጋት ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የአባልነት ድርድር 6ኛው ዙር የስራ ቡድን ስብሰባ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

አስቀድሞ በታቀደው መሰረትም የድርድር ሂደቱን እ.ኤ.አ ማርች 2026 ዓ.ም በካሜሩን /ያውንዴ/ በሚካሄደው የድርጅቱ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ለማጠናቀቅ ያለማቋረጥ እንደሚቀጥል መነጋገራቸውን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም