ከኃያላኑ ጀርመን እና ስፔን ማን ለሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ማን ያልፍ ይሆን? 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/ 2017 (ኢዜአ)፦ 14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር በጀርመን እና ስፔን መካከል ዛሬ ይደረጋል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሌትዚግሩንድ ስታዲየም ይከናወናል።

ጀርመን በሩብ ፍጻሜው ፈረንሳይን በመለያት ምት 6 ለ 5 በማሸነፍ አራት ውስጥ ገብታለች።

የብሄራዊ ቡድኑ ድል አሸነፈ በሚባል ብቻ የሚታለፍ አይደለም። አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ10 ሰው ተጫውቶ ያሸነፈበት ጥንካሬ እና ስነ ልቦና አድናቆት አስችሮታል።

በአንጻሩ ስፔን የውድድሩን አዘጋጅ ስዊዘርላንድን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ ገብታለች።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስምንት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ጀርመን አምስት ጊዜ ባሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ላይ ነበር።

የነሐስ ሜዳሊያ ለማግኘት በተደረገው ጨዋታ ጀርመን በወቅቱ የብሄራዊ ቡድን ጁሊያ ግዊን ጎል ስፔንን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ሁለቱ ሀገራት በዓልም እና አህጉራዊ የሴት እግር ኳስ ውድድሮች ውስጥ በስኬት ያሸበረቀ ታሪክ ያላቸው ናቸው።

ጀርመን ስምንት ጊዜ የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫን በማንሳት ፍጹም የበላይነት ይዛለች።

ስፔን ወደዚህ ውድድር የመጣችው የወቅቱ የሴቶች ዓለም ዋንጫ እና የዩኤፋ ሴቶች ኔሽንስ ሊግ አሸናፊ በመሆን ነው። ቡድኑ ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ሴቶች ዋንጫን አንስቶ አያውቅም።

የመከላከል አይበገሬነት፣ በመለያ ምቶች የማሸነፍ ጥንካሬ እና ለታክቲክ ተገዢ የሆነ የአጨዋወት ዘይቤ የጀርመን የሻምፒዮናው ዋንኛ መገለጫዎች ናቸው።

ቁልፍ ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት ማጣት እና በኮከብ ተጫዋቾች ላይ ብቻ የተንጠለጠለው የመፍጠር አቅም የቡድኑ ድክመቶች ሆነው ይነሳሉ።

ስፔን የቴክኒክ እና ክህሎት የበላይነት፣ ኳስን በፍጥነት ከተጋጣሚ ቡድን ተጭኖ መቀበል እና ስብስቡ ወጣቶችና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀላቅሎ መያዙ የጥንካሬ ምንጮቹ ናቸው።

የተከላካይ ክፍል መስመሩ ተጋላጭነት፣ አካል ብቃት ላይ ያመዘነ ተጋጣሚ ሲያገኝ መቸገር፣ በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ጥገኛ መሆን፣ የአጨራረስ ድክመት እና የቆሙ ኳሶች ተጋላጭነት እንደ ድክመቶች ይነሱበታል።

የእግር ኳስ ባለሙያዎች በታክቲክ የታጠረ ጨዋታ ይሆናል የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ እና ተቀራራቢ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የ46 ዓመቷ ብራዚላዊ ተጋባዥ ዳኛ ኤዲና አልቬስ ባቲስታ ተጠባቂውን ፍልሚያ በመሐል ዳኝነት ትመራለች።

የጨዋታው አሸናፊ በፍጻሜው ከእንግሊዝ ጋር ይገናኛል። እንግሊዝ ትናንት በመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጣልያንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም