ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከልና ሰላምን ለማፅናት ሚናችንን እናጠናክራለን -የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከልና ሰላምን ለማፅናት ሚናችንን እናጠናክራለን -የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 16/2017 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከልና ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ "ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፥ ሰላም ለግለሰብ፣ ለማህበረሰብና ለሀገር ደህንነት መጠበቅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ሀገር የምትጸናው በሰላም ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ባህል፣ በዜጎች ቅቡልነት ላይ የተመሰረተ ሀገረ መንግስት ለመገንባትም ሆነ ለፖለቲካዊ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት እና ስልጡን የፖለቲካ ምህዳር ለሀገር ልማት ቀጣይነትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሀገሪቱ በሁሉም መስክ ወደ እድገት ጎዳና የምታደርገውን ጉዞ ለማሳካት አስተማማኝ ሰላም በመገንባት ሂደት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ግጭትን በዘላቂነት ለማስቀረት የፖለቲካ ፓርታዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በማስረዳት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠንካራ ዴሞክራሲ መሰረት ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገራዊ የፖለቲካ ሪፎርሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በፓርቲዎች መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህል መጎልበቱንም ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱም የሀገርን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማዳበር የላቀ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።