ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁልፍ ሚና አላቸው-የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁልፍ ሚና አላቸው-የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 16/2017 (ኢዜአ):-ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁልፍ ሚና አላቸው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ "ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገንን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፤የፖለቲካ ፓርቲ እና የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮች ታድመዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት፥ ከለውጡ ወዲህ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አወንታዊ ሰላምን ለማጎልበት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አውስተዋል።
የሰላም ሚኒስቴርም በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በተወሰኑ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ውይይትና የህግ ማስከበርን በማከናወን በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሰላም መስፈኑን ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ስልጡንና በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ዴሞክራሲያዊ ምህዳርን በመፍጠር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የመሪነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።