ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብር ያስፈልጋል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 16/2017 (ኢዜአ):-ለኢትዮጵያውያን ባህልና ዕሴት የሚስማማ ዴሞክራሲን በጋራ ለመቀመር የፓርቲዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብርም እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ "ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮች ታድመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሰላም ለኢትዮጵያውያን ልማትን፣ ፍትሕንና ደስታን ያለምንም ዕንቅፋት የማግኘት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገራችን ታሪክ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፤ ግጭትና መፈናቀል የሰላምን እንቅፋት ሆነው መኖራቸውን አንስተዋል።

የለውጡ ዋናው ስትራቴጂ በጉልበት የሚደረጉ ኋላቀር የፖለቲካ ባህልና የሰላም ችግር አፈታት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላምን ለማፅናት የተፈጥሮንም ሆነ የሰውንም ጉልበተኝነት በጋራ መግራት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ዓባይን ገርተን ለኃይል ማመንጫ እንደተጠቀምነው ሁሉ ሌሎችንም የተፈጥሮን ጉልበተኝነትን ገርተን ለልማትና ለብልጽግና ማዋል አለብን ነው ያሉት።

የሰውን ጉልበተኝነት በሞራል፣ በትምህርትና በሕግ መግራት እንደሚያስፈልግ በማንሳት የሰለጠነ ፖለቲካ ለመገንባትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ተልዕኮ ሁለቱን ያልተገሩ የኢትዮጵያ ፈተናዎች መፍታት መሆን አለበት ብለዋል።


 

የሰለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበረ ሕዝብ እና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን የተረዱ ልሂቃንን እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያውያን ባህልና ዕሴት የሚስማማ ዴሞክራሲን በጋራ መቀመር እንደሚገባ በማንሳት የፓርቲዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የዴሞክራሲ ባህልን በመገንባት ጉዳይ ሁላችንም በትብብር በመሥራት አርአያ ሆነን ማሳየትም አለብን ብለዋል።

ጠመንጃ እና ጡንቻ ዴሞክራሲን አይገነቡም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ግጭት ቀስቃሽነት፣ አኩራፊነት፣ ጽንፈኝነት እና እኔ ብቻ ባይነት አላስፈላጊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ተቀብለው ላበረከቱት አዎንታዊ ሚናም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ የተፈጠረውን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት፣ ዘላቂ ለማድረግና የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት የሚያደርገውን ሚናም አድንቀዋል።

የሰላም አጀንዳ በማንገብ አዲስ የፖለቲካ ልምምድ ለመፍጠር የጀመሩትን ጥረትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

መንግሥት ለሰላም ሁሌም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፥ የፖለቲካ ኃይሎችም ሰላምን ለማጽናት በሚደረገዉ ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን አዎንታዊ አበርክቶ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም