ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሰጠችው ትኩረት በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል-ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሰጠችው ትኩረት በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል-ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/ 2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሰጠችው ትኩረት በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መምጣቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከሰው ዘር መገኛነቷ ባለፈ የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ናት።
ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ የሚታዩና የሚዳሰሱ ቅርሶቿ ፣ ታሪኮቿና እሴቶቿ በአግባቡ ባለመተዋወቃቸው ዘርፉ ለአገር ምጣኔ ሀብት የነበረው አስተዋፅኦ ከቁጥር የሚገባ አልነበረም።
ይሁንና ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በአስር ዓመቱ የልማት ግብ ትኩረት ከተሰጣቸው ዋና ዋና ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ሆኗል።
በዚህም ነባር ቅርሶች ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ታድሰዋል፣ በርካታ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችም ለምተዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተጠናቀቀው በጀት አመት በኮንፍረንስ ቱሪዝም የተገኙ ስኬቶችን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ሥራዎችም ለዘርፉ መነቃቃት ምቹ መደላደል መፍጠራቸውንም አንስተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ባልተለመደ ሁኔታ ከ150 በላይ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን አስተናግዳለች።
በየዓመቱ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ጉባኤ ጨምሮ በየደረጃው በተካሄዱ ኮንፈረንሶች የአገራት መሪዎችን ፣ የአለምአቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችንና የተለያዩ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች መስተናገዳቸውንም ነው የተናገሩት።
ኮንፈረንስ ቱሪዝም በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃትና የአገርን በጎ ገፅታ ለመገንባት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትኩረት የሰጠችው ለምን ይሆን ለሚለው ጥያቄ ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት ምላሽ ቱሪዝም ከሚፈልጋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ትራንስፖርት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲሁም መስተንግዶ ዋነኞቹ መሆናቸውን ያብራራሉ።
ኢትዮጵያም ለዚህ ምቹና አስተማማኝ መሰረተ ልማት መዘርጋቷ፣ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ለስኬቱ መገኘት አበርከቶ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም በቅርቡ ወደ ስራ የገቡት አድዋ መታሰቢያና ሳይንስ ሙዚየም፣ አዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ባለቤት መሆኗ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ አድርጓታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት በሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ መምጣታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
በመንግስት ትኩረት የተሰጠው ኮንፈረንስ ቱሪዝም በዘርፉ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከማሳደግ በላይ የአገርን በጎ ገፅታ እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተፈላጊና ተመራጭ ሆና እንድትቀጥል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
በተለይም በርካታ ቁጥር ያላቸው እንግዶች በሚሳተፋበት ኮንፈረንስ የበጎ ፍቃደኛ አስተባባሪዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር የጀመራቸው ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ መንግስት ይህንኑ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንግዶች በቆይታቸው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉና ተመልሰው መምጣት እንዲናፍቁ አመርቂ አገልግሎት በመስጠት የአገራቸውን ገፅታ ለመገንባት በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
2017 ዓ.ም ሳይጠናቀቅ ከሚካሄዱ አለምአቀፍ ኮንፈረንሶች መካከል ከሳምንት በኋላ የሚጀመረው የተመድ የሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ እና በጷጉሜ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ይገኙበታል።