እንግሊዝ ለፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝ ጣልያንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሳለች።

ማምሻውን በጄኔቭ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የ34 ዓመቷ አጥቂ ባርባራ ቦናንሴያ በ33ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ግብ ከመረብ ላይ ያሳረፈችው ግብ ጣልያንን መሪ አድርጎ ነበር።

ጣልያን አሸነፈች ሲባል በ96ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሚሼል አጂንማንግ ያስቆጠረችው ግብ እንግሊዝን አቻ አድርጋለች።

ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ ተጨማሪ ሰዓት አምርቷል።

በጭማሪ ሰዓት ክሎዊ ኬሊ በ119ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ እንግሊዝ አሸንፋለች።

ኬሊ ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት የጣልያኗ ግብ ጠባቂ  ላውራ ጁሊያኒ ብታድንባትም የተመለሰውን ኳስ አስቆጥራለች።

እንግሊዝ ፍጹም ቅጣት ምት ያገኝበት መንገድ አጨቃጫቂ ነበር።

የጣልያኗ ኤማ ሴቬሪኒ እና የእንግሊዟ ቤት ሚድ ኳስ ለማግኘት በሄዱበት አጋጣሚ በተፈጠረው ንክኪ በክሮሺያዊቷ ዳኛ ኢቫና ማርቲኒች የተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት ጣልያንን አስቆጥቷል።


በጨዋታው እንግሊዝ ኳስን በመቆጣጠር እና ተጭኖ በመጫወት የተሻለች የነበረች ቢሆንም ለረጅም ጊዜ የጣልያንን የተከላካይ መስመር ሰብራ ለመግባት ተቸግራ ነበር።

የወቅቱን የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ እንግሊዝን ለፍጻሜ አልፋለች።

የዋንጫ ክብሯን ለማስጠበቅ ከጀርመን እና ስፔን አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

ጣልያን በአውሮፓ ሴቶች አውሮፓ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የማለፍ ህልሟ አልተሳካም።

ጀርመን እና ስፔን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም