ፌዴሬሽኑ በዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ላይ የወሰደው ቆራጥ እርምጃ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በተሞክሮ የሚወሰድ ነው- ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ በዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ላይ የወሰደው ቆራጥ እርምጃ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በተሞክሮ የሚወሰድ ነው- ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ላይ የወሰደው ቆራጥ እርምጃ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በተሞክሮ የሚወሰድ ነው ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ገለጹ።
በናይጄሪያ አቡኩታ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛው የአፍሪካ ከ20 እና 18 ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የልዑካን ቡድኑ መሪ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ አትሌቶቹ ስለነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢንስትራክተር አድማሱ በብዙ ችግር ተፈትነው መልካም ውጤት ላመጡት አትሌቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለልዑክ ቡድኑ እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት መልካም መሆኑን አንስተዋል።
ፌዴሬሽኑ በዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ላይ የወሰደው ቆራጥ እርምጃ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክሎም በተተኪ አትሌቶች ላይ ፌዴሬሽኑ በትኩረት እንደሚሰራ በማንሳት ፣ለዓመታት ችግር ሁኖ የቆየው የትራክ እና የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ 2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 5 ነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎችን ማግኘቷን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ከሻምፒዮናው አስቀድሞ በናይጄሪያ በተካሄደው 31ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ኢትዮጵያ በእድሜ ተገቢነት ላይ ለወሰደችው እርምጃ ምስጋና የተቸራት ሲሆን ይህ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን ተነስቷል።