ናይጄሪያ ለፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ናይጄሪያ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 1 በማሸነፍ የፍጻሜውን ትኬት ቆርጣለች።

ማምሻውን በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም በተካሄደው ተጠባቂ ፍልሚያ ራሼዳት አዲባጄ በፍጹም ቅጣት ምት እና ሚሼል አሎዚ በጨዋታ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሚሼል አሎዚ በ94ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ግብ ናይጄሪያን ያስፈነጠዘ በአንጻሩ የደቡብ አፍሪካን ልብ የሰበረ ሆኗል።

ሊንዳ ሞትሃሎ ለደቡብ አፍሪካ ብቸኛዋን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ  ላይ አሳርፋለች።

ጠንካራ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራት ቢሆንም ናይጄሪያ የግብ እድሎችን በመፍጠር ብልጫውን ወስዳለች።

ውጤቱን ተከትሎ የዘጠኝ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናይጄሪያ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ አልፋለች።

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካ ክብሯን የማስጠበቅ ጉዞ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ተገቷል።

ናይጄሪያ በፍጻሜው ከሞሮኮ እና ጋና አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር አዘጋጇ ሞሮኮ ከጋና ጋር ምሽት 4 ሰዓት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም