ቀጥታ፡

አርሶና አርብቶ አደሮች መሬታቸውን አስይዘው ከባንክ የሚበደሩበት አዲስ የፖሊሲ ለውጥ ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበትን ዕድል እየፈጠረ ነው - የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው አርሶና አርብቶ አደሮች መሬታቸውን አስይዘው ከባንክ የሚበደሩበት አዲስ እሳቤ በማምጣት ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበትን እድል እየፈጠረ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የግሉን ዘርፍ ተዋናዮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማሳተፍ በዘላቂ ልማት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊና በንግድ ዙሪያ የሚመክር የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግል ዘርፍ መድረክ ተካሂዷል፡፡


 

የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ ለአካታች ፋይናንስና ልማት የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት ከባቢ በኢትዮጵያ እና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው ብዝሃ ዘርፎች መካከል ግብርና አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርናን ወድ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር የሚል ሀሳብ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ትኩረት ግን በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ መዋቅራዊ ሽግግር ሲባል አርሶና አርብቶ አደሩን ከእጅ ወደ አፍ ምርት ወደ ትርፍ አምራችነት ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የግብርና ድርሻ የሚይዙት አርሶና አርብቶ አደሮች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግብርና ስርዓታቸውን ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡

የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬታቸውን አስይዘው ከባንክ የሚበደሩበት አዲስ እሳቤ በማምጣት ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበትን እድል እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች በዚህ የፖሊሲ እርምጃ የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውንም ተናገረዋል፡፡

አርሶ አደሮች በበሬ እያረሱ ግብርናውን ማዘመን አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስት ከ500 በላይ የሜካናይዜሽንና መስኖ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውሰጥ እንዲገቡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሮች በአነስተኛ ማሳ ላይ ብቻቸውን መሥራት አዳጋች መሆኑን ገልጸው፤ ባለሃብቶች በአዋጅ በጸደቀው በግብርና ምርት ውል መሰረት ተጣምረው መስራት እንደሚችሉ አስረድተዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም