ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምርትና ምርታማነት ዕድገትን በዘላቂነት የሚያስቀጥል ነው-የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርትና ምርታማነት ዕድገትን በዘላቂነት የሚያስቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በዚህም የተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ችግኝ ተክለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ አረንጓዴ አሻራ ከዘላቂ ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።

መርሃ ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተመዘገበ ያለውን የምርትና ምርታማነት ዕድገት በዘላቂነት የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዜጎች በምቹና ጤናማ አካባቢ እንዲኖሩ ከማስቻሉ ባለፈ ለመጪው ትውልድ ስነ ምህዳሩ የተጠበቀ ምቹ አካባቢ የማሸጋገር ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ ችግኝ ከመትከሉ ባሻገር የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ አመርቂ ተግባር እያከናወነ መሆኑን በመጥቀስ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከሚተከሉት የፍራፍሬ ዘሮች መካከል የአቮኮዶ ችግኝ የአካባቢ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅና የህብረተሰቡን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞችና አመራሮች ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ተክለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም