በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

የዘጠኝ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናይጄሪያ እና የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ደቡብ አፍሪካ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም የሚያካሂዱት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።

ናይጄሪያ በሩብ ፍጻሜው በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ዛምቢያን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።

ቡድኑ በውድድሩ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም።

ተጋጣሚዋ ደቡብ አፍሪካ በሩብ ፍጻሜው በሴኔጋል ተፈትና በመለያ ምት 4 ለ 1 በማሸነፍ የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብታለች።


 

ደቡብ አፍሪካ በአራቱ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናት አንድ ጊዜ አቻ ወጥታለች።ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ አንድ ግብ አስተናግዳለች።

የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ተቀናቃኝ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች እስከ አሁን 13 ጊዜ ተገናኝተው ናይጄሪያ 7 ጊዜ ስታሸንፍ ደቡብ አፍሪካ 3 ጊዜ አሸንፋለች። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ናይጄሪያ በጨዋታዎቹ 11 ግቦችን ስታስቆጥር ደቡብ አፍሪካ  7 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ሁለቱ ቡድኖች በአስገራሚ ሁኔታ በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው ናይጄሪያ 8 ጊዜ ስታሸንፍ ደቡብ አፍሪካ 2 ጊዜ ድል ቀንቷታል።

እ.አ.አ በ2000 እና 2018 በተካሄዱት የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ለፍጻሜ ተገናኝተው ናይጄሪያ በሁለቱም ጨዋታ አሸንፋለች።

ሞሮኮ እ.አ.አ በ2022 ባዘጋጀችው 12ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ደቡብ አፍሪካ 2 ለ 1 ያሸነፈችበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀናቃኝነታቸው እየጋለ የመጣው ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉት ጨዋታ “ታሪካዊ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

አስፈሪ የአጥቂ መስመር ያላት ናይጄሪያ እና የመሐል ክፍሏ ጠንካራ የሆነው ደቡብ አፍሪካ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር አዘጋጇ ሞሮኮ ከጋና ጋር ምሽት 4 ሰዓት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሩብ ፍጻሜው ሞሮኮ ማሊን 3 ለ 1፣ ጋና አልጄሪያን በመለያ ምት 4 ለ 2 አሸንፈዋል።


 

ሁለቱ ቡድኖች በውድድር እና ወዳጅነት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሞሮኮ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ጋና ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷታል። 

ሞሮኮ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ጋና 7 ግቦችን አስቆጥራለች።

የግማሽ ፍጻሜ አሸናፊዎቹ  ቅዳሜ ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ያልፋሉ። ተሸናፊዎቹ አርብ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም